ኢሳት (ሚያዚያ 19 ፥ 2008)
የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ኦኬሎ አኳይን ጨምሮ ሰባት ተከሳሾች በተመሰረተባቸው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ከሰባት እስከ ዘጠኝ አመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ተቀጡ።
ተከሳሾች የቀረበባቸውን ወንጀል እንዳልፈጸሙ በመግለጽ የመከላከያ ማስረጃን በማቅረብ ሲከራከሩ ቢቆዩም ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች ያቀረቡት ማስረጃ የሚያስተባብል አይደለም ሲሉ ውድቅ ማድረጉም ታውቋል።
የተከሳሾች ጉዳይ ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤቱ የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ ሰባቱ ተከሳሾችን ጋምቤላን ለመበተንና ከፌዴሬሽን ለመገንጠል ሞክረዋል ሲል በቀረበባቸው ክስ ጥፋተኛ ሲል ወስኖባቸዋል።
በዚሁ ውሳኔ መሰረትም አቶ ኦኬሎና ተከሳሽ ዴቪድ ኡጁሉ በዘጠኝ አመት ጽኑ እስራት የተቀጡ ሲሆን፣ ቀሪ አምስት ግለሰቦችም በሰባት አመት ፅኑ እስራት ተቀጥተዋል።
ከሁለት አመት በፊት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት እነዚሁ ተከሳሾች በጋምቤላ ክልል የመሳሪያ የትጥቅ ትግልን ለማካሄድም በተለያዩ ሃገራት እንቅስቃሴን ሲያደርጉት ቆይተዋል ሲል አቃቤ ህግ በክሱ ማስቀመጡን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የቀድሞ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድርም በስልጣን ጊዜያቸው በአኙዋክና በኑዌር ብሄረሰብ አባላት መካከል ግጭትን እንዲባባስ በማድረግ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ሞት ምክንያት መሆናቸውንም የቀረበባቸው ክስ ያስረዳል።
ይሁንና የቀድሞ ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች የቀረበባቸውን ወንጀል እንዳልፈጸሙ በመግለጽ የመከላከያ ማስረጃን ቢያቀርቡም ፍርድ ቤቱ ማስረጃው ራሱን ማስተባበል የሚያስችል አይደለም በማለት የፍርድ ውሳኔን እንዳስተላልፉ ለመረዳት ተችሏል።