ሚያዚያ ፲፰(አሥራ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከ 2 ሺ በላይ ቤቶችን ለማፍረስ በዝግጅት ጋር ያለው የክልሉ መንግስት፣ ዛሬ ከህዝብ ጋር ተፋጦ መዋሉን ወኪላችን ገልጿል። ህዝቡ “ከ10 አመታት በፊት ቤቶችን ስንሰራ ዝም ብላችሁ አሁን ለምን እርምጃ ለመውሰድ ተነሳችሁ? በክረምት ቤተሰቦቻችንን ሜዳ ላይ መበተን ሰብአዊነት ነው ወይ? ለምን ቤቶቹን ህጋዊ አታደርጉልንም?” የሚሉ ጥያቄዎችን ሲጠይቅ የቆዬ ቢሆንም፣ መልስ ሊያገኝ አልቻለም።
በሸንኮር መስተዳደር ስር በሚገኙ አካባቢዎች 1 ሺ ያላነሱ ቤቶች እንደሚፈርሱ የገለጸው ወኪላችን ፣ ዛሬ ሸንኮር መስተዳድራና በድሬ ጥያራ መለያ ቦታ ላይ በሚገኘው ድልድይ ላይ ነዋሪዎች ቋጥኝ ድንጋይ እያንከባለሉ መንገዶችን የዘጉ ሲሆን፣ ይህን አልፎ በሚመጣ ላይ እርምጃ እንወስዳለን በማለት በመናገር ላይ ናቸው።
ቤቶቹ የሚፈርሱት በሸንኮር ወረዳ፣ ከአቡበክር ወረዳ፣ ከሃኪም ወረዳ እንዲሁም ከሶፊ ወረዳ ናቸው። ጊዮርጊስ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ቤት አፍራሽ ግብረሃይል ቤት ማፍረስ የጀመረ ሲሆን፣ ህዝቡ ቀኑን ሙሉ በጩከት ተቃውሞውን ሲገልጽ ውሎአል። አንድ አዛውንት የጎረቤታቸው ቤት ሲፈርስ አይተው በድንጋጤ ህይወታቸው ማለፉ ታውቋል።
ቤቶቻቸው የሚፈርሱባቸው ሰዎች በየአመቱ ግብር ይገብሩ እንደነበር ነዋሪዎች በማነጋገር ወኪላችን ከላከው መረጃ ለመረዳት ይቻላል።