ኢሳት (ሚያዚያ 18 ፥ 2008)
ሁለት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በመኪና ተገጭተው መሞታቸውን ተከትሎ፣ በጋምቤላ ከተማ የቀጠለው ግጭት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና የሌሎች ግብረ-ሰናይ ድርጅቶችን እንቅስቃሴ እያወከ መገኘቱ ታወቀ። የደቡብ ሱዳን ኑዌር ተወላጆች ከካምፕ ወጥተው በኢትዮጵያውያኑ ላይ ያደረሱት ጥቃት ለመበቀል የተንቀሳቀሱት ወገኖች፣ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ንብረቶች ላይ ጭምር ጥቃት ማድረሳቸው ተመልክቷል።
አክሽን አጌንስት ሃንገር (ACF) የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ሾፌር ሁለት የኑዌር ተወላጅ የሆኑ ደቡብ ሱዳናውያንን ገጭቶ መግደሉ፣ በካምፕ የሚገኙ ስደተኞችን ማስቆጣቱ ተመልክቷል። እነዚህ ስደተኞች በበቀል ተነሳስተው የመኪና ሾፌር ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ብቻ በኢትዮጵያውያኑ ላይ ጥቃት መሰንዘራቸውና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ግድያ መፈጸማቸው ተመልክቷል። የግብረ ሰናይ ድርጅት ሰራተኞችም የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ታውቋል።
ሁለቱ ደቡብ ሱዳናውያን ሴቶች በመኪና ተገጭተው በመሞታቸው ተቆጥተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰራተኞች የሆኑ ኢትዮጵያውያን ጭምር ያጠቁት የደቡብ ሱዳን ስደተኞች በኢትዮጵያውያኑ የአጸፋ ጥቃት ሲሰነዘርባቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ንብረቶችም ጉዳት እንደደረሰባቸው ታውቋል። ሃሙስና አርብ በተከታታይ ቀናት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በርካታ ተሽከርካሪዎች መኖሪያ ስፍራዎች ተጠቅተዋል።
በሁለቱም ወገን የሚሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ የተባበሩት መንግስታት ግቢ በፖሊሶች በመጠበቅ ላይ ይገኛል።
ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን መገደላቸውንና 108 ህጻናት መታገታቸውን ተከትሎ በጋምቤላ የተፈጠረው ውጥረት አሁንም የቀጠለ ሲሆን፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች አሁንም እንደተዘጉ ቀጥለዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም በደቡብ ሱዳን ውስጥ ለተፈጠረው ቀውስ በምክንያትነት የሚጠቀሰው የአማጺው ቡድን መሪና የቀድሞ ምክትል ፕሬዚደንት ሪክ ማቻር ዛሬ ማክሰኞ ደቡብ ሱዳን ጁባ ገብተዋል። ግምቱ በሽምግልና ለመፍታት በተደረገ ጥረት የምክትል ፕሬዚደንት ስፍራ ተሰጥቷቸው የተመለሱት ዶ/ር ሪክ ማቻር ደቡብ ሱዳን ነጻነቷን ከተጎናጸፈበት እኤአ 2005 እስከ 2013 በምክትል ፕሬዚደንትነት ማገልገላቸው ይታወቃል።