ኢሳት (ሚያዚያ 13 ፥ 2008)
የደቡብ ሱዳን መንግስት በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ ግድያን የፈጸሙ ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃን ለመውሰድ መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ሃገሪቱ እወስደዋለሁ ያለችው ይኸው ወታደራዊ እርምጃ ከኢትዮጵያ መከላከልያ ሰራዊት ጋር በጥምረት እንዲሚካሄድ የደቡብ ሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለፁን ሱዳን ትሪቢዩን ዘግቧል።
በ13 መንደሮች የተፈጸመው ጥቃት በሺዎች በሚቆጠሩና ከባድ መሳሪያን በታጠቁ የሙርሌ ጎሳ ታጣቂዎች መከናወኑንም ጋዜጣው የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ በዘገባው አስፍሯል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች አብዛኛዎቹ የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሰራዊት የደንብ ልብስን የለበሱ እንደነበርና የኢትዮጵያ መንግስት ላይም በአማጺ ቡድኖች ላይ ጥርጣሬ እንደሌለው መግለጹን ሱዳን ትሪቢዩን አስነብቧል።
የኢትዮጵያና የደቡብ ሱዳን መንግስታት በታጣቂ ሃይሉ ላይ ሊወስዱ ባሰቡት ወታደራዊ ዘመቻ ላይ ለመምከርም የደቡብ ሱዳን መከላከያ ሰራዊት ሃላፊ ጄኔራል ፖል ማሎንግ በቀጣዮቹ ቀናቶች ወደ አዲስ አበባ እንደሚጓዙም ለመረዳት ተችሏል።
የደቡብ ሱዳንን ድንበር ለመዝለቅ ፈቃድን ስትጠብቅ የነበረችው ኢትዮጵያ በጥቃቱ ወቅት 60 ታጣቂዎችን መግደሏን መገለጿም ይታወሳል።