ኢሳት (ሚያዚያ 13 ፥ 2008)
11 የአሜርካ ሴናተሮች የኢህአዴግ መንግስት የአገሪቷን ህገ-መንግስቱን በመጠቀም ሃሳባቸውን በገለጹት ሰላማዊ ሰልፈኞች፣ ጋዜጠኞች፣ እና የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት ላይ እያደረሰ ያለውን የጉልበትና የጠብ-አጫሪነት እርምጃ በጽኑ አወገዙ።
የሜሪላንድ ግዛት ሴናተር ቤን ካርዲን፣ እንዲሁም ሲናተር ሩቢዮ ሌሎች 9 ሴናተሮች ለአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጽ/ቤት በጻፉት ደብዳቤ፣ ህወሃት/ኢህአዴግ ፈጽሟል የተባለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ግድያ የአሜርካ መንግስት እንዲያጣራ ጠይቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስትም በተዋዋሚዎች፣ ጋዜጠኞችና፣ የሲቪክ ማህበረሰብ አባላት ላይ የሚወስደውን እርምጃ በአስቸኳይ እንዲያቆም ሴናተሮቹ ሲጠይቁ፣ በግፍ የተገደሉ ሰዎችን የሚያጣራ ገለልተኛ መርማሪ ቡድን እንዲያቋቁምና፣ የአለመረጋጋት መንስዔ የሆኑትን የአገዛዙና ሌሎች ቡድኖችና ግለሰቦች ተጠያቂ እንዲደረጉ መክረዋል።
“የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ የወሰዱት እኩይ እርምጃ እጅግ አስደንግጦኛል፣ ለሟች ቤተሰቦችም የሃዘን መልዕክት ማስተላለፍ እፈልጋለሁ” ያሉት ሴናተር ካርዲን፣ የኢትዮጵያ ህገመንግስት ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹና ሰላማዊ የሆነ ሰልፍ ማድረግ እንዲችሉ ቢፈቅድም በሰልፈኞቹ ላይ የተወሰደው እርምጃ ግን በፍጹም ተቀባይነት የለውም ብለዋል። ሴናተር ካርዲን የኢትዮጵያ መንግስት እኤኣ በ2009 ጸረ-ሽብር ህጉንና የመያዶ ድርጅቶችን ህግ ሲያወጣ የመናገር ነጻነትንና ተቃዋሚዎችን ለመደፍጠጥ እንጂ ስለዲሞክራሲ ተጨንቆ አይደለም በማለት የኢትዮጵያ መንግስት ለዴሞክራሲ ቁርጠኛ አቋም አለመያዙን ተናግረዋል።
ሴናተር ሩቢዮ በበኩላቸው “ ሰላማዊ ሰልፈኞች ሃሳባቸው በመግለጻቸው ብቻ ታስረዋል፣ ሰቆቃ ተፈጽሞባቸዋል፣ እኔም ይህንን የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሰረታዊውን የኢትዮጵያን ህዝብ መብት የሚቃረን በመሆኑ በጽኑ አወግዛለሁ ብለዋል። የኦባማ አስተዳደርም የአሜርካ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሲነጋገር ለሰብዓዊ መብቶች ቅድሚያ እንዲሰጥ አጥብቀው ጠይቀዋል።
አሁን ባለው ድርቅና የድንበር ችግር፣ የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቦችን ከማግለል ይልቅ ለማቀራረብ ጥረት ቢያደርግ ይሻለዋል ያሉት ሴናተር ካርዲን፣ የኢትዮጵያ መንግስት ከደረሰበት ችግር ሊወጣ የሚችለው መሰረታዊ የዜጎችን የሰብዓዊ መብቶችን ሲያከብር ብቻ ነው።
የሜሪላንዱን ሴናተር ካርዲንና ሲናተር ሩቢዮን ደግፈው በኢትዮጵያ ላይ የመፍትሄ ሃሳብ ለአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የጻፉት ሴናተር ማሪኣ ካንትዌል፣ ሴናተር ክርስቶፈር ኩንስ፣ ሲናተር ዲክ ዱርቢን፣ ሴናተር አል ፍራንከን፣ ሴናተር አምይ ክሎቡቻር፣ ሴናተር ፓትሪክ ሊህ፣ ሴናተር ኤድዋርድ ማርኬይ፣ ሴናተር ቦብ ማነንዴዝ፣ ሴናተር ፓትይ መሬይ እና ሴናተር ሸርውድ ብራውን ናቸው።
አሜርካ ሽብርተኝነትን በአፍሪካ ቀንድ ለመዋጋትና የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሃይል ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ጋር አብራ እንደምትሰራ ይታወቃል። ኢትዮጵያ በሱማሊያ አልሻባብን ለማባረር ባደረገቸው ውጊያ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገዝንዘብ እንደተሰጣትና ሌሎች ወታደራዊ ስልጠናዎችን ጭምር እንዳገኘች ዘገባዎች ያመለከታሉ።