ሚያዚያ ፲፫(አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ባወጣው መግለጫ ፣ በኦሮሚያ ክልላዊ መስተዳድር ዉስጥ ያለዉን ሕዝባዊ መነሳሳት ለማዘናጋትና ለማዳፈን ሲል መንግስት በሚቆጣጠራቸዉ የዜና ማሰራጫዎች ተጎጂ የሆነዉን ሕዝባችንን በይበልጥ ለመጉዳት ታስቦ በሚመስል መልኩ ሰፊ የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ ተከፍቷል ብሎአል።
መንግስት መልካም አስተዳደርን ያጓደሉ ናቸዉ በማለት በመጀመሪያ 300 ባለሥልጣኖችን አሁን በቅርቡ ደግሞ 863 ባለሥልጣኖችንና ኃላፊዎችን ከሥልጣን አባርሬአለሁ በማለት መንግስት ተደጋጋሚ መግለጫ ቢሰጥም ለኦሮሞ ሕዝብ የሚጠቅም አንዳች ጠብታ ነገር የለዉም ብሎአል።
ሕዝቡን የጎዳዉና እየጎዳም ያለዉ አብዮታዊ ዲሚክራሲ ወይም ልማታዊ ዲሞክራሲ የተባለዉ የኢህአዴግ የፖለቲካ ፍልስፍና እንጂ የግለሰቦች ከሥልጣን መዉረድም ሆነ ሥልጣን ላይ መዉጣት ብዙም ትርጉም አይኖረዉም፣ ስለሆነም ብሔራዊ ዕርቅ በአገሪቱ ዉስጥ ሰፍኖ መላዉ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን በሠላም ኖረዉ በአገራቸዉ ሁለንተናዊ ጉዳይ ዉስጥ በነፃነት ተሳትፎ ለማድረግ ሲችሉ ብቻ ስለሆነ ይኼዉ እንዲመቻች እንጠይቃለን ብሎአል፣ ኦፌኮ።
ኦፌኮ በማያያዝም ፣ በፊንፊኔ ዙሪያ ይኖር የነበረዉ አርሶ አደር ወገኖቻችን ሁሉንም ዜጎቻችንን ተጠቃሚ ባላደረገ ኢንቬስትመንት ስም ከነባር ቀዬያቸዉ እንዲፈናቀሉ ሲገደዱ የቤተሰቦቻቸዉ ኑሮ ወደልመና እንዲገፋ ተደርጓል፣የሚለው ኦፌኮ፣በቂ ካሳ እንዳልተከፈላቸዉ እየታወቀ ከቅርብ ቀናት ወዲህ ደግሞ ላለፈዉ መፈናቀል ካሳም ባይከፈልህ ተደራጅና ዕርዳታ ይፈለግልሃል እየተባለ መገኘቱ፣ ድርጊቱ በዜጎች ቁስል ላይ እንጨት የመስደድ ያህል ስለሆነ፤ ዜጎችን በደካማ ጎን መዉጋት እንዲቆምና ዜጎች ዘላቂ መፍትኼ የሚያገኙበት ሁኔታ እንዲመቻች አበክረን እናሳስባለን ብሎአል።
የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንና የኦሮሚያ ከተሞችን አስመልክቶ ጠቃሚ ነገር ተሰርቶ ሕዝብ እምቢ በማለቱ የተወሰኑ አንቀጾችን በማሻሻልና የተወሰኑ አንቀጾችን ደግሞ ሰርዘናል የሚባለዉ ሕዝብን የመሸንገል ድርጊት የትም የማያደርስ ስለሆነ አዋጁ ሙሉ በሙሉ እንዲሰረዝ ፣ ለመልካም አስተዳደር መጓደል ተጠያቂዉ ኢህአዴግ እና ኢህአዴግ የሚመራዉ መንግስት መሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተደጋግሞ የተገለጸ ቢሆንም ዛሬም ድረስ የኦሮሞን ዜጋ መግደል፣ ማሰር፣ ማሳደድና ማወክ አለመቅረቱን የገለጸው ኦፌኮ፣ በቅርቡ ሚያዚያ 5/2008 ከሰዓት በኋላ 10፡00 ሰዓት አከባቢ እንጂነር በዳዳ ገልቹ ፊጎ፤ የኦዶ ሻክሶ ወረዳ ነዋሪ እና ሚያዚያ 9/2008 ደግሞ ለሙ ነጋሽ ጢጣ የተባለ የሆሮ ጉዱሩ ነዋሪ ከቀኑ በ6፡00 ሰዓት ላይ በመንግስት ታጣቂ ኃይሎች መገደላቸውን ጠቅሷል።
አብዛኛዉ የኦሮሞ ወጣቶች ክፍል ገብተዉ ባልተማሩበት ሁኔታ ዉስጥ የሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ እና የመሰናዶ ትምህርት ፈተናዎች ሊሰጡ ቀናት ብቻ መቅረታቸውን በማስታወስ፣ በእስር ላይ የሚገኙ ፖለቲከኞች፣ ተማሪዎችና መምህራኖቻቸዉ ተፈትተዉ በተዛባ ፖሊሲና ያልተገባ እርምጃ አወሳሰድ ምክንያት የተስተጓጎለዉ የትምህርት ጊዜ ቢያንስ እስከ ነሐሴ ወር 2008 አጋማሽ ድረስ ተራዝሞ፣ የኦሮሞ ወጣቶች ተረጋግተዉ ፈተናዉን ሊቀመጡ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻችም ኦፌኮ በመግለጫው አስታውቋል።