ሪክ ማቻር ወደደቡብ ሱዳን ጁባ ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ ተራዘመ

ኢሳት (ሚያዚያ 10 ፥ 2008)

መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ አድርገው የነበሩት የደቡብ ሱዳን አማጺ ቡድን መሪ ሪክ ማቻር በጋምቤላ ክልል በኩል አድርገው ወደ ደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ ልያደርጉት የነበረው ጉዞ ተራዘመ።

የልተጠበቀ ነው የተባለው የአማጺ ቡድኑ መሪ መዘግየት በጋምቤላ ሊያጓጉዝ የነበረው አውሮፕላን የጉዞ ማስተካከያ ማድረጉን ጁባ አውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያ ማቻርን በመጠባበቅ ላይ ለነበሩት ጋዜጠኞች አስታውቀዋል።

ላለፉት አንድ አመት ያህል መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ከተማ አድርገው የነበሩት ሪክ ማቻር ወደጁባ በመመለስ የምክትል ፕሬዚደንትነት ስልጣናቸውን ይረከባሉ ተብሎ ይጠበቃል።

የአማጺ ቡድኑን መሪ ጉዞ መስተጓጉል ያስታወቁት ቃል-አቀባዩ  ሪክ ማቻር ምን አልባት ማክሰኞ ወደ መዲናይቱ ጁባ ሊመለሱ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

በሳምንቱ መገባደጃ አርብ በጋምቤላ ክልል በታጣቂዎች ተፈጽሟል በተባለ ጥቃት ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ከ100 የሚበልጡ ነዋሪዎችም ታፍነው መወሰዳቸው ተነግሯል።

በ60 የጥቃቱ ፈጻሚዎች ላይ እርምጃን እንደወሰደ የገለጸው የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ወደጎረቤት ደቡብ ሱዳን ግዛት በመግባት ድርጊቱን በመፈጸሙ ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቱን አስታውቀዋል።

የደቡብ ሱዳን መንግስትም ሆነ አማጺያን በጋምቤላ ክልል ስለደረሰው ጥቃት የሰጡት ምላሽ የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የደቡብ ሱዳኑ አማጺ ቡድን መሪ ሪክ ማቻር በጋምቤላ ክልል ሊያደርጉት የነበረው ጉዞ የተራዘመው ለጠባቂዎቻቸው የመሳሪያ ፈቃድ ከኢትዮጵያ በኩል ባለመገኘቱ መሆኑን የአማጺ ቡድኑ ሃላፊዎች ገልጸዋል።

የሱዳን ህዝቦች የነጻነት ነቅናቄ ቃል አቀባይ የሆኑት ማቢዮር ጋራንግ የሪክ ማቻር የግል ጠባቂዎች መሳሪያን ይዘው ወደ ጋምቤላ ለመጓዝ ያደረጉት ሙከራ ከፈቃድ ጋር በተገኛኘ አለመሳካቱን ለመገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።

የአማጺ ቡድኑ ሃላፊዎች ለማቻር መዘግየት ነው ያሉትን ምክንያት በመግለጽ ላይ ቢሆኑም የተለያዩ አካላት ማቻርን ከደቡብ ሱዳን ወደ ጋምቤላ ይዞ ይጓዝ የነበረው አውሮፕላን ፈቃድ ሳያገኝ መቅረቱን በመግለጽ ላይ ናቸው።

ይሁንና የኢትዮጵያ መንግስት ለማቻር አውሮፕላን በምን ፈቃድ እንደከለከለ የአማጺ ቡድኑ ሃላፊዎች የሰጡት መረጃ አለመኖሩን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ሪክ ማቻር ወደጋምቤላ ክልል ከገቡ በኋላ ጉዟቸውን ወደጁባ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።