በሜዲትራኒያን ባህር ከሰጠሙት ስደተኞች አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ታወቀ

ኢሳት (ሚያዚያ 10 ፥ 2008)

እሁድ ሚያዚያ 9 ፥ 2008 ዓም ከግብፅ ተነስተው ወደ ጣልያን ሲጓዝ ከነበሩትና በሜዲትራኒያን ባህር ውስጥ ከሰጠሙት 400 ስደተኞች መካከል አብዛኞቹ ኢትዮጵያውያን መሆናቸው ተገለጸ። ህይወታቸውን ያጡት ወጣቶች ከሃገራቸው የተሰደዱት ምክንያትም ከዚህ አመት ከህዳር ወር ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የኦሮሚያ ተቃውሞ የተነሳ መንግስት የሚወስደውን የሃይል እርምጃ ሸሽተው መሆኑን የሟች ቤተሰቦች ለኢሳት ገለጹ።

እሁድ እለት የሶማልያ መገናኛ ብዙሃን እና ማህበራዊ ድረገጾች ስለአሰቃቂው የጀልባ አደጋ መረጃ ካወጡ በኋላ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን ዘገባ አቅርበዋል።

አሰቃቂውን ዜና ተከትሎ የቤተሰቦቻቸውንና የጓደጆቻቸውን ሞት የተረዱት ኢትዮጵያውያን በግብጽ ዋና መዲና ካይሮ የተለያዩ መንደሮች ለቅሶ መቀመጣቸው ታውቋል።

በሃዘን ላይ ካሉት መካከል የአራት ቤተሰቦችና ጓደኞቹን ሞት የተረዳው አወል አብዱልዋህብ የተባለ ኢትዮጵያዊ ከሳምንት በፊት የሸኛቸውን ፎዚያ ጄይላን አብዱሰላም ጣሂር፣ ሙንተዘም ሃጂሁሴንና፣ አብዲሳ ባርሾ የአደጋው ሰላባ መሆናቸውን ገልጿል።

አብዱልሰላም ጣሂር የ19 ዓመት፣ አብዲሳ ባርሾ የ21 ዓመትና፣ ሙንተዛም ሃጂሁሴን የ20 ዓመት እንዲሁም ፎዚያ ጄይላን 21 ዓመት ዕድሜ የነበራቸው ወጣቶች መሆናቸውን ተገልጿል። ።

በአደጋው ከሞቱት 200 በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን መካክል አብዛኞቹ የባሌ፣ የድሬዳዋና የሃረር ተወላጆች መሆናቸው ታውቋል።

አብዛኞቹ ወጣቶች በኦሮሚያ በሚካሄደው ህዝባዊ ንቅናቄ በመንግስት የሚፈጸመውን ግድያና እስር በመሸሽ የተሰደዱ መሆናቸውን አራት ቤተሰቦቹንና ጓደኞቹን በጀልባ አደጋ ያጣው አወል ለኢሳት ገልጿል።

ስደተኛ ኢትዮጵያውያን በካይሮ የሚገኘው የተባበሩት መንግስታት ስደተኞች ኮሚሽን ጉዳያቸውን ለማመልከት የ3 አመት ቀጠሮ የሚሰጥ መሆኑ ትዕግስታቸውን እያሟጠጠ ህይወታቸውን አደጋ ለሚያጋልጥ ውሳኔ እንዳደረሳቸው ለመረዳት ተችሏል።

በኦሮሚያ ከህዳር ወር ጀምሮ እየተካሄደ ባለው ህዝባዊ አመጽ ከ350 በላይ ዜጎች በመንግስት መከላከያ ሰራዊት መገደላቸውና ከ5000 በላይ መታሰራቸው ይታወቃል።

ብዙ ሺ ኢትዮጵያውያን በሃገራቸው አምባገነናዊ አገዛዝ ስራ-አጥነትንና ድህነትን በመሸሽ በተለያዩ ሃገራት በየዕለቱ እንደሚሰደዱ ዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት (IOM) በተደጋጋሚ ባወጣቸው ሪፖርቶች ሲገልጽ ቆይቷል።