ሚያዚያ ፲(አሥር) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኦሮምያ የተነሳውን ህዝባዊ ተቃውሞ በሃይል መቆጣጠራቸውን የሚናገሩት የኦህዴድ ኢህአዴግ ታማኝ ካድሬዎች፣ ከትናንት ወዲያ ሚያዚያ 8 ቀን 2008 ዓም በቦረና ገላና ወረዳ ቶሬ ወረዳ የ26ኛውን የኦህዴድ በአል እናከብራለን በሚል ሰበብ፣ ከጡዋቱ 3 ሰአት ተኩል እስከ ቀኑ 11 ሰአት ተኩል በአየር ላይ ጥይት እየተኮሱ ደስታቸውን ሲገልጹ፣ በተዘዋዋሪም ህዝቡን ሲያሸብሩ ውለዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት አመጸኞችን ልክ ልክ አስገባናቸው በሚል ስሜት የተኩስ እሩምታ ሲያሰሙ ቢውሉም፣ ህዝቡ ግን ድርጊታቸው በቁጭትና በንቀት ይመለከት ነበር፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በአካባቢው መንግስት የሚያካሂደው የሚዲያ አፈናና ጥቃት ተጠናክሮ በመቀጠሉ አለማቀፉ ማህረሰብ ፈጥኖ እርምጃ እንዲወስድ የአፍሪካ ቀንድ የሰብአዊ መብት ሊግ ባወጣው መግለጫ ገልጾአል፡፡