ኢሳት (ሚያዚያ 7 ፥ 2008)
አለም-አቀፍ የስደተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) በድርቅ ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያን የሚሆን እርዳታና ቁሳቁስ እያቅረበ መሆኑን አስታወቀ። የአለም-አቀፍ የስደተኞች ድርጅት በቅርቡ 442 የመጠለያ ፕላስቲክ፣ የወባ መከላከያ አጎበር፣ ፍራሽ፣ ብርድ ልብስና፣ ለቤት አስፈላጊ የሆኑ ሌሎች ቁሳቁሶች በአፋር ክልል በዱብቲ፣ ሚሌና፣ አሳይታ ወረዳዎች ለሚኖሩ ወገኖች ማቅረቡን አስታውቋል። በሚሌ 87, በዱብቲ 305 እና በአሳይታ 50 በድርቅ ምክንያት የተፈናቀሉ ቤተሰቦች እደተረዱ እንደሆነ ይኸው የስደተኞች ድርጅት ለዜና አውታሮች በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በከብቶቻቸው ዕርባታ ላይ ህይወታቸውን የመሰረቱት በአፋር ክልል የሚኖሩ አርብቶ አደሮች በድርቁ ሳቢያ ከብቶቻቸው ስለሞቱባቸው ቀያቸውን ጥለው አጎራባች አማራ፣ ኦሮሚያና፣ ትግራይ ክልሎች እየተሰደዱ እንደሆነ ታውቋል።
አለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ከአለም አቀፉ ቀይ መስቀል ድርጅት ጋር በመተባበር በአማራ፣ አፋር፣ ጋምቤላ፣ ኦሮሚያ ደቡብ ህዝቦች፣ ሶማሌ እና ትግራይ ክልሎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች እርዳታ እያደረገ እንደሆነም ገልጿል። በ 2016 የፈረንጆች አመትም፣ ከ800ሺ በላይ የሚሆኑ ዜጎች የመጠለያ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ የቁሳቁስ እርዳታዎች እንደሚፈልጉም ተመልክቷል።