ኢሳት (ሚያዚያ 7 ፥ 2008)
ከአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገነው የአምቦ ከተማ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከውሃ እጥረት ጋር በተገናኘ ያቀረቡትን ተቃውሞ ተከትሎ በአምቦ ዩኒቨርስቲ አዲስ ግጭት ተቀሰቀሰ።
በተማሪዎች መቅረብ የጀመረውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር የጸጥታ ሃይሎች በተማሪዎቹ ላይ ድብደባ መፈጸማቸውንና በዩኒቨርስቲው የመማር ማስተማር ሂደቱም ተስተጓጉሎ እንደሚገኝ እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።
በከተማዋ ለበርካታ ጊዜያት የተከሰተውን የውሃ እጥረት ተከትሎ የአምቦ ዩኒቨርስቲ ለተማሪዎች የምግብ አገልግልሎት ለማቅረብ ባለመቻሉ ምክንያት ተማሪዎቹ አቅርቦቱ እንዲስተካከል ከቀናት በፊት ጥያቄ መቅረብ መጀመራቸውም ታውቋል።
ይሁንና፣ በአካባቢው ሰፍረው የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች በአምቦ ዩኒቨርስቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ በመግባት በተማሪዎቹ ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን ነዋሪዎች አስተድተዋል።
ለደህነታቸው ሲሉ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት እነዚሁ እማኞች የአምቦ ከተማ ከሃሙስ ጀምሮ በከፍተኛ የጸጥታ ሃይሎች ቁጥጥር ስር መሆኗንና ድርጊቱ አዲስ ውጥረት አስፍኖ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
የአምቦ ከተማ “በወታደራዊ አገዛዝ ውስጥ የምትገኝ ናት” ሲሉ የገለጹት እማኞች መንግስት በየጊዜው የሚነሱ ማህበራዊ ጥያቄዎችን በሃይል ለመቆጣጠር እያደረገ ያለው እርምጃ በነዋሪው ዘንድ አለመረጋጋትን አስፍኖ መሰንበቱንም ተናግረዋል።
ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተገናኘ ተቀስቅሶ የነበረ ተቃውሞ በአምቦ ከተማና ዩኒቨርስቲ ውስጥ በርካታ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸው የሚታወስ ሲሆን፣ አሁንም ድረስ መኖራቸውን የተለያዩ አካላት ይገልጻሉ።
በነጻነት ወጥተን በነጻነት መግባት አንችልም ያሉት የከተማዋ ነዋሪዎች በየዕለቱ በትንሹ 10 የሚሆኑ ሰዎች ለእስር እየተዳረጉ መሆኑንም ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ አስታውቀዋል።
በአምቦ ዩኒቨርስቲ ከውሃ እጥረቱ ጋር በተያያዘ የቀረበውን ተቃውሞ ለመቆጣጠርም የጸጥታ ሃይሎች አስለቃሽ ጢስ መጠቀማቸውንና አርብ ምሽት ድረስ ዩኒቨርስቲው አለመረጋጋት ውስጥ መሆኑን እማኞች አክለው አስረድተዋል።
በከተማዋ ያለው ውጥረት እልባት ባለማግኘቱም በተማሪዎች ላይ የደረሰን ጉዳት በአግባቡ ለማወቅ መቸገራቸውን እማኞች ተናግረዋል።