ሚያዚያ ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ጠ/አቃቤ ህግ ሚኒስቴር መ/ቤት የተሙዋላ ተቁዋማዊ ነጻነት እንደሚኖረው በአዋጁ መግቢያ ላይ የተጠቀሰ ቢሆንም ክስ ማንሳትን በተመለከተ የጠ/ሚኒስትሩ ፈቃድ እንዲጠየቅ መደንገጉ፣ የተቁዋሙን ነጻነት ከወዲሁ ጥያቄ ላይ ጥሎታል። በአዋጁ አንቀጽ 6 ንኡስ አንቀጽ ሰ ላይ እንደተመለከተው ጠቅላይ አቃቢ ህግ “የፌዴራል መንግስትን በመወከል የወንጀል ጉዳዮች ክስ ይመሰርታል፣ ይከራከራል፣ ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ጠቅላይ ሚኒስትሩን በማማከር ክስ ያነሳል፣ የተነሳ ክስ እንዲቀጥል ያደርጋል” በሚል ተቀምጦአል።
በአዋጁ አንቀ16 ንኡስ አንቀጽ 1 ደግሞ በተቃራኒው የአቃቤ ህግ የሙያ ነጻነት ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንደሚከናወን ሲደነግግ፣ “የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ስልጣንና ተግባሩን ሲያከናውን ከማንኛውም ሰው ወይም አካል ጣልቃ ገብነት ነጻ ሆኖ በህግ መሰረት ይፈጽማል” ይላል። የጠ/ሚኒስትሩ በአማካሪነት ስም የተቀመጠ ጣልቃገብነት የዚህኑ አዋጅ ድንጋጌ የጣሰ መሆኑን ዘጋቢያችን የህግ ባለሙያዎችን አስተያየት ዋቢ በማድረግ ዘግቦአል፡፡
አንዳንድ የህግ ባለሙያዎች ይህ አንቀጽ ጠ/ሚኒስትሩ በአቃቤ ህጉ የእለት ተእለት ስራ ጣልቃ እንዲገቡ ከመፍቀዱ በተጨማሪ የስራ መጉዋተትን ያስከትላል፣ የተቁዋሙንም የስራ ነጻነት ይጎዳል በሚል ከወዲሁ እየተቹት ይገኛሉ።
በተጨማሪም የመንግስት መ/ቤቶች በተናጠል የሚከታተሉትን የፍትሀብሄር ክሶች ወደአቃቤ ህግ መጠቃለሉ ፣ መ/ቤቱ ከአቅሙ በላይ ስራዎች እንዲወጠር እድል የሚሰጥ፣ የህዝብን ጥቅም የሚጎዳ ውሳኔ ነው በማለት ተቃውመውታል።
መንግስት ጠቅላይ አቃቢ ህግን ከፍትህ ሚኒስቴር በማውጣት ራሱን ችሎ በተቁዋም ደረጃ እንዲወቀር አድርጎአል፡፡