አርባ ስድስት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በማላዊ ተያዙ

ሚያዚያ ፯(ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በትናትናው እለት ድንበር አቋርጠው ካለ ሕጋዊ ቪዛ ወደ ማላዊ የገቡ አርባ ስድስት ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን መያዙን የአገሪቱ ፓሊስ አስታወቀ።
በሚዚምቢ አውራጃ ኢኳንዳ በሚባል አካባቢ በትምባሆ እርሻ ውስጥ ተደብቀው ባሉበት በአካባቢው ነዋሪዎች ጥቆማ ስደተኞቹ መያዛቸውንና በአሁኑ ወቅትም በሙዙዙ እስር ቤት ውስጥ እንደሚገኙ የፓሊስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ማርቲን ቡማናሊ ገልፀዋል።
በቁጥጥር ስር የዋሉትን ኢትዮጵያዊያን ስደተኞችን ወደ ኢሚግሬሽን ስደተኞች ጉዳይ እንደሚተላለፉ ቃል አቀባዩ ገልጸው፣ ሕዝቡ ከፓሊስ ጋር በመተባበር ሕገወጥ ስደተኞችን ለመቆጣጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፎ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።
በማላዊ ባሁኑ ወቅት ያለው የሕገወጥ ስደተኞች እንቅስቃሴ መቀነሱንም ማላዊ 24 አክሎ ዘግቧል።
ኢትዮጵያ ባለ ሁለት አሃዝ ኤኮኖሚያዊ ለውጥ ማምጣትዋን የገዥው ፓርቲ በየቀኑ ቢናገርም፣ ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በነጻነት፣በስራ ዋስትና ማጣትና፣ የአገራቸውን መጻኢ እጣ ፈንታ በመፍራት የማትተካ ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው በአራቱም ማእዘናት መፍለሳቸውን አላቋረጡም።