ኢሳት (ሚያዚያ 6 ፥ 2008)
በአፍሪካ ሃገራት የብሄረሰብ ጥያቄ የቅራኔና የግጭት ምክንያት መሆኑ እያበቃ ቢመጣም፣ በኢትዮጵያ ግን ችግሩ መቀጠሉ ተገለጸ። ከየትኛውም የአፍሪካ ሃገር ምናልባትም በአለም ላይ ጭምር የብሄረሰብ ጥያቄን መሰረት ያደረጉ የመገንጠል እንቅስቃሴዎች እየተካሄደ የሚገኙት በኢትዮጵያ ብቻ መሆኑን የአፍሪካ የስትራቴጂና ጸጥታ ተቋም ዋና ስራ-አስፈጻሚ ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ገልጹ።
አፍሪካ ኢንቲትዩት ፎር ስትራቴጂክ ኤንድ ሴኩሪቲ ስተዲስ የሚባለውንና በአፍሪካ የጸጥታ ሁኔታ ላይ ጥናት የሚያደርገውን ተቋም የሚመሩት ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ዛሬ የአፍሪካውያን ችግር ድንበር ዘለል ወንጀሎችና ሽብር እንጂ የብሄረሰብ ጥያቄ እንዳልሆነ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አብራርተዋል።
450 ያህል ቋንቋ የሚነገርባቸው ኮንጎን የመሳሰሉ ሃገራት ጭምር በሃገራቸው ውጥረት አርግበውና ሰላምን አውርደው በስምምነት የሚኖሩበት ሁኔታ መፈጠሩንም አብራርተዋል።
የከፍተኛ ተቋም ትምህርታቸውን አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና በአሜሪካ ኒውዮርክ ኮሎምቢያ ዩኒቨርስቲ ያጠናቀቁት ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ በደርግ መንግስት ውስጥ በምክትል ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዲሁም በዕርዳታ ማስተባበሪኣይ ኮሚሽን ኮሚሽነርነት አገልግለዋል።
በኢትዮጵያ በተከሰተው አስከፊ የ1977ቱ ድርቅ ወቅት ምዕራባውያንን በመለመን እንዲሁም አለም አቀፍ ዝና የተጎናጸፉት እነ ማይክል ጃክሰን “We are the World!” የሚለውን ሙዚቃ ለኢትዮጵያ ርሃብ ሲያቀነቁንና ዕርዳታ ሲያሰባስቡ የሂደቱ መሪ ተዋናይ የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ያኔ መጀመሪያ ርሃቡን ለመደበቅ የተደረገው ሙከራ ያስከተለውን ጉዳት አስታውሰው፣ ዛሬም ለማለባበስ የሚደረገው ሙከራ ውጤቱ አስከፊ እንደሚሆን አሳስበዋል።
ችግሩን ማመን አደጋውን ለማቋቋም የሚያስችል ተቋም መመስረትን በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ ባለሙያዎችን በመቅረብ ዘላቂ መፍትሄ መሻት አስፈላጊ መሆኑም አሳስበዋል።
በቀድሞው የደርግ መንግስት ም/የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በኋላም የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ የነበሩትን ስርዓት አውግዘው ከተለዩበት ጊዜ ጀምሮ ላለፉት 30 ዓመታት ያህል በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና መሰል አለም አቀፍና አህጉራዊ ተቋም ውስጥ በአማካሪነትና በተመራማሪነት ሲሰሩ መቆየታቸውን ለመረዳት ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት በዋና ስራ አስፈጻሚነት የሚመሩት አፍሪካ ኢንስቲትዩት ፎር ስትራቴጂክ ኤንድ ሴኪዩሪቲ ስተዲስ በአፍሪካ ሃገራት በጠቅላይ ሚኒስትርነት እንዲሁም በሌሎች ከፍተኛ የስልጣን ቦታዎች ላይ የነበሩ ባለሙያዎች በአባልነትና በሃላፊነትና የታቀፉበት ተቋም መሆኑን መረዳት ተችሏል።