የፍትህ ሚኒስቴርን ህልውና እንዲያከትም የሚያደርገው ረቂቅ አዋጅ ጸደቀ

ኢሳት (ሚያዚያ 6 ፥ 2008)

የፍትህ ሚኒስቴርን ህልውና እንዲያከትም የሚያደርገውን ከበርካታ የህግ ባለሙያዎች ዘንድ ትችት ሲቀርበት የቆየው የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ረቂቅ አዋጅ ሃሙስ በፓርላማ ጸደቀ።

የአዋጁ መጽደቅ የፍትህ ሚኒስቴርን እንዲፈርስ የሚያደርግ ሲሆን የህግ ባለሙያዎች ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለብቻቸው ተቋቋሞ የፍትህ ሚኒስቴር እንዲቀጥል ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ሃሙስ ህግ ሆኖ የፀደቀው የፌዴራል ጠቅላ አቃቤ ህግ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን የበርካታ የፍትህ ጉዳዮችን በበላይነት እንደሚቆጣጠርም ታውቋል።

ይኸው አዲሱ ተቋም መንግስትን በመወከል የወንጀል ጉዳዮች ላይ ክስን የመመስረት ስልጣን ሲኖረው የተነሱ ክሶችም እንዲቀጥሉ የማድረግ ስልጣን ተሰጥቶታል።

የሚመሰረቱ ክሶች ሃገራዊ ይዘት በሚኖረው ጊዜም የፌደራሉ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማማከር ክስን የመመስረትና የማንሳት ስልጣንም እንዲኖረው በህጉ መካተቱን ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።

ይሁንና የህግ ባለሙያዎች አቃቢ ህግ ራሱን ለመመስረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲያማክር መደረጉ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ክፍተትን እንደሚፈጥር ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ የንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት የግልግል ዳኝነት ተቋም ሃላፊና የህግ ባለሙያ የሆኑት አቶ ዮሃንስ ገብርዔል “ጠቅላይ አቃቤ ህግ ከስራ አስፈጻሚው ጋር አብሮ ቁጭ ብሎ ህግ ያስከብራል ብዬ አላምንም” ሲሉ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንም በዚሁ የፌዴራል አቃቤ ህግ ስር እንዲጠቃለል የተደረገ ሲሆን፣ የህግ ባለሙያዎች ድርጊቱ ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ ላይ ናቸው።

ህጉ እስከሚጸድቅ ድረስ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠሪነቱ ለጊዜው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ የህጉ መጽደቅን ተከትሎ ኮሚሽኑ ወደ አቃቢ ህግ ስር መጠቃለሉ ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩም በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚጸድቁ ጠቅላይ አቃብያን ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል።