ከ20 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን የምግብ እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ተመድ ገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 5 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ የተከሰተው ድርቅ እየባሰና እየተስፋፋ በመቀጠል ከህዝቡ 1/5ኛው ወይንም 20 ሚሊዮን ያህሉ የምግብ እርዳታ ጠባቂ ማድረጉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ። በታህሳስ ወር ላይ በድርቅ ተጠቂ የነበሩት 429 ወረዳዎች ቢሆኑም በአሁኑ ወቅት የድርቅ ሰለባ የሆኑ ወረዳዎች ቁጥር በ 14 ጨርሞ 443 መድረሱንም የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን በመጥቀስ ብሉምበርግ ዘግቧል።

በድርቁ በከፍተኛ ደረጃ የተጠቁ ወረዳዎች ቁጥር በ18 በመቶ ጨምሮ ከ186 ወደ 219 ከፍ ማለቱ የተገለጸ ሲሆን፣ በ50 ዓመታት ታሪክ ውስጥ ያልታየ መሆኑም ተዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የተከስተው ሚሊዮኖች ለከፋ ችግር የተጋለጡበት የድርቅ አደጋ በምስራቅ ኢትዮጵያ በከፋ ሁኔታ መቀጠሉን ቢቢሲ ዘገበ። የቢቢሲው ዘጋቢ ኦማን ሊንጉዛ ወደ ምስራቅ ኢትዮጵያ ተጉዞ ማክሰኞ ሚያዚያ 4 ፥ 2008 ባጠናከረው ዘገባ፣ የድርቅ ተጎጂዎችን ለመርዳት ጥረት ቢኖርም፣ በቂ ምግብ እየቀረበ አለመሆኑን አመልክቷል።

በአካባቢው የነዋሪዎቹ 90 በመቶ ከብቶች በድርቁ ማለቃቸውም ከዘገባው መረዳት ተችሏል።

ኦማር የተባለ የአካባቢው ነዋሪ ለቢቢሲው ዘጋቢ እንደተናገረው ከመቶ በላይ ግመሎች፣ ፍየሎችና ላሞች የነበሩት ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ግን ሁሉም አልቀዋል። ከከብቶቹ ማለቅ ባሻገር የራሱ መጻዒ ሁኔታ እያሰባሰበ መሆኑን ለቢቢሲ ዘጋቢ ገልጿል።

ድርቅ በተስፋፋባቸው አካባቢዎች በህይወትና በጤና ለመቆየት የሚያስፈልጉ የተመጣጠኑ ምግቦች አቅርቦት በከፍተኛ ሁኔታ ማቆልቆሉንም ከዘገባው ለመረዳት ተችሏል። ሴብ ዘቺልድረን የተባለው ምግባረ ሰናይ ተቋም በመጥቀስ ቢቢሲ እንደዘገበው 6 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ህጻናት ለከፍተኛ የምግብ እጥረት ተጋልጧል።