የድርቅ መከሰትን ተከትሎ ከ600 ሺ በላይ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን ተመድ ገለጸ

ኢሳት (ሚያዚያ 5 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ ከ600ሺ በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገለጸ።

ድርቁ እያደረሰ ያለው ጉዳት እልባት ባለማግኘቱ ምክንያትም ህይወታቸውን ለመታደግ ሲሉ መኖሪያ ቀያቸውን እየለቀቁ የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሊሄድ እንደሚችልም ተሰግቷል።

በድርቁ ሳቢያ ከተፈናቀሉት ወደ 640ሺ ሰዎች መካከል አብዛኞቹ በአፋር፣ ሶማሊ እና አማራ ክልል የሚገኙ ሲሆን ከእነዚሁ መካከልም ከ135ሺ የሚበልጡ አዲስ ተፈናቃይ መሆናቸውን ድርጅቱ ገልጿል።

ባለፈው ወር ብቻ በአፋር፣ አማራ ጋምቤላ ኦሮሚያ ሶማሊ ክልሎች ከ56ሺ በላይ ሰዎች በድርቁ ሳቢያ ከቀያቸው መፈናቀላቸው ታውቋል።

ይኸው በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀየረ እንደመጣ ያስታወቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ ወደ ረሃብ ደረጃ ሊሸጋገሩ አንድ ደረጃ ብቻ የቀራቸው ወረዳዎች ቁጥር 219 መድረሳቸውን ይፋ ማድረጉም ይታወሳል።

በተለይ በሶማሌ ክልል በሚገኙ ሁለት ዞኖች ድርቁ በብዙ በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ የከፋ ጉዳትን እያደረሰ እንደሚገኝ የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ናቸው።

ከዚህ ከድርቅ አደጋ ጋር በተገናኘም የካናዳው የማሰራጫ ኮርፖሬሽን (CBC) የኢትዮጵያ መንግስት ለተረጂዎች አለም አቀፍ እርዳታን ለመጠየቅ መዘግየቱን የተለያዩ አካላት እንደገለጹ ዘግቧል።

በኢትዮጵያ የድርቅ አደጋ ዙሪያ ልዩ ልዩ ሪፖርትን ያቀረበው የማሰራጫ ጣቢያው በወቅቱ የልቀረወን የእርዳታ ጥያቄ ተከትሎም ድርቁ የከፋ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደሚገኝም ዘግቧል።

ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ወረዳዎች ቁጥርም ባለፉት ሶስት ወራቶች በ20 በመቶ አካባቢ ማድረጉንና ድርቁ የአለም አጀንዳ ሆኖ መሰንበቱን አመልክቷል።

በቅድመ ረሃብ መከላከል ዙሪያ የሚሰራ አንድ አለም አቀፍ ተቋም በኢትዮጵያ ሊከሰት የሚችለውን የድርቅ አደጋ ከአንድ አመት በፊት ይፋ አድርጎ እንደነበር መግለጹን መዘገባቸን ይታወሳል።

የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው ድርቁ በቁጥጥር ስር ዉሏል በማለት አለም አቀፍ አካላት ሲሰጡ የነበሩ ትንበያዎችን ሲያጣጥሉ መቆየታቸውም ይታወቃል።

ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ አካላት ግን መንግስት ለተረጂዎች በወቅቱ የእርዳታ ጥሪን አላቀረበም በማለት ቅሬታን እያቀረቡ እንደሚገኙ የካናዳው የማሰራጫ ጣቢያ ባቀረበው ዘገባው አመልክቷል።