ዜና (ሚያዚያ 5 ፥ 2008)
የመከላከያ ሚኒስቴር የበታች ሹሞችና መኮንኖች ባዘጋጀው የ4 ቀናት ኮንፈረንስ የሰራዊቱ መክዳት አብይ ርዕስ ሆኖ መውጣቱን ምንጮች ለኢሳት ገለጹ። ባለፈው ሳምንት የተካሄደውና ከሰኞ እስከ ሃሙስ በቀጠለው ኮንፈረንስ ከተለያዩ የሰራዊቱ ክፍሎች የተውጣቱ የበታች ሹሞችና መኮንኖች በቪዲዮ ኮንፈረንሰ ከመከላከያ ባለስልጣናት ጋር ተወያይተዋል።
አዲስ አበባ ላይ ሆነው በቪዲዮ ኮንፈረንሰ ማብራሪያና መግለጫ የሰጡት የመከላከያ ሚኒስትሩ አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ ሲሆኑ፣ ከፍተኛውን ወታደራዊ ስልጣን የያዙት ጄኔራሉ ከአጠገባቸው ቢሆኑም፣ መድረኩን ሙሉ ለሙሉ ለአቶ ሲራጅ ፈርጌሳ መልቀቃቸውንም ምንጮች አስረድተዋል።
ላለፉት 5 አመታት የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በማብራራት የጀመሩት አቶ ሲራጅ ፈርጌሳ፣ በቀጣዩ አምስት አመታት ስለሚካሄደው 2ኛ ዙር የትራንስፎርሜሽን እቅድ በማብራራት እድገት ይመጣል ሲሉ ለሰራዊቱ ቃል ገብተዋል።
በትራንስፎርሜሽን እቅድ ንግግራቸው የጀመሩት የመከላከያ ሚኒስትሩ በሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሰራዊቱ ስሜት ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ ሰራዊቱ በብዛት እየከዳ የሚገኝበትንም ምክንያት እንዲያብራሩ ለተሰብሳቢዎች መድረኩን ሰጥተዋል።
ከጦር ክፍለ ስለሰራዊቱ መክዳት ተጠንቶ የቀረበው ሪፖርት አጥጋቢ አለመሆኑንም አስረድተዋል። ከተሰብሳቢውም ስለሰራዊቱ መክዳት ይቀርብ የነበረው ሪፖርት የችግሩ ምንጭ መብራራት የነበረበትና በአስተዳደራዊ ችግሮች ዙሪያ የተድበሰበሰ እንደነበረም ተመልክቷል።
በሰራዊቱ ውስጥ እጅጉን ገንኗል ስለሚባለው የአንድ ብሄር የበላይነት በመድረክ ደፍሮ የሚናገር አለመገኘቱንም ምንጮቹ አስረድተዋል። የቀድሞ ታጋዮች የነበሩት የጦር ጄኔራሎች መድረኩን ለአቶ ሲራጅ ፈርጌሳ የለቀቁት በዚህ ዙሪያ ሰራዊቱ የሚሰማውን ይናገራል በሚል እንደሆነም ታምኖበታል።
ሆኖም ስለስብሰባው ችግር የተባሉት ጉዳዮች በተጨባጭ ሳይነቀስና በመፍትሄውም ላይ ሳይመከር መጠናቀቁ ታውቋል።