በአፋር በድርቅ የተጎዱ ነዋሪዎች ድጋፍ ባለማግኘታቸው ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል ተባለ

ኢሳት (ሚያዚያ 3 ፥ 2008)

በአፋር ለድርቅ አደጋ የተጋለጡ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ባለማግኘታቸው ምክንያት ለከፋ ችግር ተጋልጠው እንደሚገኙ ታውቋል።

በተለይ ለከፋ የምግብ እጥረት የተጋለጡ ህጻናትና በእርግዝና ላይ ያሉ እናቶች በምግብ እጥረቱ ክፉኛ ጉዳይ እየደረሰባቸው መሆኑን የአፋር የሰብዓዊ መብቶች ድርጅት ገልጿል።

በክልሉ በቀጣዮቹ ሁለት ወራቶች ውስጥ የሚጠበቀው የበልግ ዝናብ መዝነብ ካልጀመረም የሰውና የእንስሳት ሞት ሊከሰት እንደሚችል የድርጅቱ ሃላፊ አቶ ገሃስ መሃመድ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ አስረድተዋል።

በክልሉ በአምስት ዞኖች ውስጥ 32 ወረዳዎች በዚሁ የድርቅ አደጋ ክፉኛ ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሆነም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ የመለክታል።