ወደ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ኤግዚቢሽን ለመካፈል ሄደው ከሀገር እንዳይወጡ የታገዱ ሰባት በስጋ ላኪነት የተሰማሩ ዜጎችን የኢትዮጵያ መንግስት ማስለቀቅ አልቻለም።

መጋቢት ፴( ሠላሳ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ከየካቲት 13 እስከ 17/2008 አም በዱባይ ከተማ አንድ ኤግዚቢሽን ላይ ለመሳተፍ ወደስፍራው ካመራው የመንግስት ልኡካን መካከል በስጋ ላኪነት ስራ ውስጥ የነበሩ ሰባት ባለሀብቶች በሻርጂያ ከተማ ፖሊስ ተይዘው ክስ ሳይመሰረትባቸው ከታሰሩ በኋላ ፖስፖርታቸውን አስይዘው በዋስ ቢለቀቁም ከሀገር እንዳይወጡ ከታገዱ የአንድ ወር ተኩል ጊዜ አሳልፈዋል።
ባለሀብቶቹ የታገዱበት ምክንያት ከስድስት ወራት በፊት ለአንድ የዱባይ ኩባንያ ከ267 ሺ ቶን በላይ የበግ ስጋ ከላኩ በኋላ በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግስት ተበላሽቶአል በሚል እንዲወገድ መደረጉን ተከትሎ በተፈጠረ አለመግባባት ነው። ታሪን አልሁዳ የተሰኘው የዱባይ ኩባንያ ስጋው በመበላሸቱ ኢትዮጵያዊያኑ ላኪዎች የወሰዱትን ገንዘብ ከእነኪሳራው ሊመልሱልኝ ይገባል ያለ ሲሆን ኢትዮጵያዊያኑ ላኪዎች በበኩላቸው በውሉ መሰረት የተመረመረ ስጋ አስረክበናል፣ ችግርም ካለ በውሉ መሰረት በኢትዮጵያ ህግ ልንዳኝ ይገባል በሚል ሲከራከሩ ቆይተዋል።
ባለሀብቶቹ በህገወጥ መንገድ በሻርጂያ ፖሊስ ታስረው ከተፈቱ በኋላ ከሀገር እንዳይወጡ የታገዱ ቢሆንም የኢትዮጵያ መንግስት ጉዳዩን ተከታትሎ ባለሀብቶቹን ማስፈታት ባለመቻሉ ቤተሰቦቻቸው ጭንቀት ላይ መጣሉን ተናግረዋል።
ስማቸውን መግለጵ ያልፈለጉ የአንድ ታሳሪ ቤተሰብ እንደተናገሩት መጀመሪያ ጉዳዩን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይዞታል፣ እየተከታተለው ነው ተባልን፣ ምንም የተገኘ ነገር የለም። በሀላም ጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤ ጵፈዋል ብንባልም ምንም መፍትሄ ሳናገኝ ከአንድ ወር ተኩል በላይ ቤተሰቦቻችን በሰው ሀገር ታግተው ለሆቴል እየገፈገፉ ነው፣ ቤተሰቦቻችን ነገ ከነገወዲያ ወህኒ ቤት ይወረወራሉ በሚል ስጋት ተጨንቀናል ብለዋል። የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መንግስት በታገዱት ዜጎቹ ጉዳይ እያደረገ ስላለው ጉዳይ እስካሁን በይፋ የሰጠው መግለጫ የለም።