ኢትዮ-ቴሌኮም ያልተቀረጡ ስልኮችን በአገልግሎት ላይ እንዳይውሉ የሚያደርግ ቁጥጥርን ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

ኢሳት (መጋቢት 28 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ የስልክ አገልግሎትን በብቸኝነት እየሰጠ የሚገኘው ኢትዮ-ቴለኮም በተለያዩ መንገዶች ወደ ሃገሪቱ የገቡና ያልተቀረጡ ስልኮችን በአገልግሎት ላይ እንዳይውሉ የሚያደርግ ቁጥጥርን ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።

ኢኪዩፕመንት አይደንቲቲ ሬጂስተር የተሰኘ ቴክኖሎጂን አገልግሎት ላይ ለማዋል በዝግጅት ላይ የሚገኘው ድርጅቱ በሃገሪቱ ያሉ ሁሉ የእጅ ስልኮች ምዝገባ እንደሚያደርጉም ገልጿል።

በምዝገባው ያልተካተቱና በስጦታና በተለያዩ መንገዶች ወደ ሃገር ውስጥ የገቡ ስልጎችም ተገቢው ምርመራ ካልተካሄደባቸው በስተቀር በአገልግሎት ላይ እንዳይዉሉ የሚደረግ መሆኑን የኢትዮ-ቴሌኮም ሃላፊዎች ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ይፋ አድርገዋል።

በተለያዩ መንገዶች ወደሃገሪቱ የገቡና በአገልግሎት ላይ የሚገኙ ስልኮችም በምን መልኩ ህጋዊ መደረግ እንዳለባቸው ከቀናት በኋላ ጉዳዩ የሚመከለታቸው አካላት ምክክርን ያካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።