ኢሳት (መጋቢት 28 ፥ 2008)
በህገ-ወጥ ንግድ ተሰማርታችኋል የተባሉ 120 ነጋዴዎች በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ስር ዋሉ።
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ባለፉት 30 ቀናት ብቻ በቁጥጥር ስር የዋሉት እነዚሁ ነጋዴዎች ያለ-ደረሰኝ ግብይትን ሲፈጽሙ ቆየተዋል ሲል ረቡዕ አስታውቋል።
ባለስልጣኑ 85 አምራቾች፣ አስመጪዎችና የጅምላ አከፋፋይ ድርጅቶች ላይ ድንገተኛ ዘመቻ ማካሄዱን አውስቶ ከ85ቱ የንግድ ድርጅቶች መካከል 77 የሚሆኑት ያለ-ደረሰኝ ግብይት ሲፈጽሙ መገኘታቸውን ይፋ እንዳደረገ ከሃገር ቤት ከተገኘ መረጀ ለመረዳት ተችሏል።
ባለስልጣኑ ነጋዴዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ቢገልጽም ክስ ይመስርት አይመስርት ግን ያስታወቀው ነገር የለም።
በዚሁ ድንገተኛ ዘመቻ ክትትል ከተደረባቸው መካከል 90 በመቶ የሚሆኑ በህገ-ወጥ ተግባር ላይ ተሰማርተው መገኘታቸውን ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱን ባለስልጣኑ አክሎ ገልጿል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ጀምሮ በርካታ ነጋዴዎችና ባለስልጣናት በህገ-ወጥ ንግድ ተሰማታችኋል ተብለው በቁጥጥር ስር መዋላቸው ይታወሳል።