መጋቢት ፳፮( ሃያ ስድስት ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በሶማሊ ክልል ዋና ከተማ ጅጅጋ መጋቢት 26፣2008 ዓም ሌሊት የጣለውን ዝናብ ተከትሎ ከ100 በላይ ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ የአካባቢው ነዋሪዎች ሲገልጹ፣ መንግስት በበኩሉ 13 ሰዎች መሞታቸውንና ከ55 በላይ ደግሞ የደረሱበት ባለመታወቁ ፍለጋ እየተካሄደ መሆኑን ገልጿል።
እሁድ እኩለሌሊት ላይ የጣለው ድንገተኛ ዝናብ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 8 ሰዎች በጎርፍ ተወስደዋል። በርካታ ህጻናት በተኙበት ጎርፍ እንደወሰዳቸው የከተማው ነዋሪዎች በሃዘን ተውጠው ተናግረዋል።
በከተማው መሃል የሚያልፈው ቆዱን ወዳ የተባለው ወንዝ ሞልቶ ወደ መኖሪያ ቤቶች በመፍሰሱ ጉዳት መከተሉን ነዋሪዎች ተናግረው፣ ሼክ አብዱሰላም መሰናዶ ትምህርት ቤት ሙሉ በሙሉ በጎርፍ ወድሟል።
የአካባቢው ነዋሪዎች መንግስት የጉዳቱን መጠን አሳንሶታል በማለት ወቀሳ እያሰሙ ነው።