በኦሮሚያ ባለፉት ሶስት ሳምንታት ብቻ  ከሶስት ሺ በላይ ሰዎች ታሰረዋል ተባለ

ኢሳት (መጋቢት 23 ፥ 2008)

አራተኛ ወሩን የያዘው በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰው ተቃውሞ መቀጠሉንና ባለፉት ሶስት ሳምንታት ብቻ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎች ለእስር መዳረጋቸውን ሮይተርስ የተለያዩ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ አርብ ዘገበ።

የመንግስት ባለስልጣናት በክልሉ ተፈጽሞ ለነበረው ሞትና ጉዳት ይቅርታን ቢጠይቁም በክልሉ እስራቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን የተለያዩ አካላት ለዜና አውታሩ አስታውቀዋል።

የዚሁ የጸጥታ ሃይሎች የእስር ዘመቻ 2ሺ 600 ሰዎች ባለፉት ሶስት ሳምንታት ብቻ ለእስር መዳረጋቸውን የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያው አንድነት (መድረክ) አመልክቷል።

የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች እየወሰዱት ያለው የእስር ዘመቻ ተቃውሞን ለማፈን ያለመ መሆኑንና በ12 የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች መካሄዳቸውን ሮይተርስ የፓርቲውን መግለጫ ዋቢ በማድረግ በዘገባው አቅርቧል።

በተያዘው ሳምንት የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በክልሉ ያለው ተቃውሞ እልባት አለማግኘቱንና ወደ 3ሺ የሚጠጋ ሰው ለእስር መዳረጉን ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ መግለጻቸው ይታወሳል።

በቅርቡ ለፓርላማ ሪፖርትን ያቀረቡት ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በክልሉ ተፈጽሟል ላሉት ጥፋት ይቅርታን በመጠየቅ ተቃውሞው እልባት አግኝቷል ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ይሁንና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማትና የፓርቲ አመራሮች እንዲሁም ነዋሪዎች ተቃውሞው አሁንም ድረስ በተለያዩ መልኮች ቀጥሉ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።

እነዚሁ ተቃውሞን ኣያሰሙ የሚገኙ የክልሉ ነዋሪዎች በተለያዩ ከተሞች ሰፍረው የሚገኙ የጸጥታ ሃይሎች ከክልሉ እንዲወጡና ለእስር የተዳረጉ ሰዎችም እንዲፈቱ ጥያቄን እያቀረቡ እንደሚገኝ ከሃገር ቤት ይተገኘ መረጃ አመልክቷል።