ኢሳት (መጋቢት 21 ፥ 2008)
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች መፍትሄ ያልተገኘለትን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥራትና መቆራረጥ ለመቅረፍ አንድ የህንድ ኩባንያ የ50 ሚሊዮን ዶላር (የ1.2 ቢሊዮን ብር) ፕሮጄክት ተረከበ።
ለተመሳሳይ ተግባር ከአንድ አመት በፊት የ16.7 ሚሊዮን ዶላር ስምምነት ፈርሞ የነበረው የህንዱ ፓወር ግሪድ ኮርፖሬሽን ለችግሩ መፍትሄን አላመጣም ተብሎ የሁለት አመት ኮንትራቱ ሳይረዝም ከሃገር መሰናበቱ ይታወሳል።
በመጀመሪያው ዙር የስራ አፈጻጸም ደስተኛ ያልነበሩ የመንግስት ባለስልጣናት የህንዱ ኩባንያ የተጠበቀውን ያህል ውጤት ባለማስመዝገቡ ምክንያት ኮንትራቱ እንዲያቋርጥ መደረጉን መግለጻቸው ይታወሳል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገረሚካዔል ከህንዱ ኩባንያ ጋር የተቋረጠውን ውል ተከትሎ ስራውን በሃገር ውስጥ ባለሙያዎች ይከናወናል ሲሉ ማስታወቃቸውም የሚታወቅ ነው።
ይሁንና በመዲናይቱ አዲስ አበባ ከተማና በሌሎች ክልሎች ያለው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥራትና መቆራረጥ ተባብሶ በመቀጠሉ ምክንያት መንግስት ላርሰን ኤንድ ቶሮቦ ሊሚትድ ከተሰኘ ሌላ የህንድ ኩባንያ ጋር አዲስ የ1.2 ቢሊዮን ብር (50 ሚሊዮን ዶላር) ስምምነትን ፈጽሟል።
በሁለት አመት ውስጥ ተግባራዊ ይደረጋል የተባለው ይኸው ፕሮጄክት የባቡር መስመሮችን ጨምሮ ለኢንዱስትሪዎችንና በሌሎች ደንበኞች የኤሌክትሪክ ሃይልን ያለማቋረጥ እንዲደርስ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ከህንዱ ኩባንያ ጋር የተደረገው ስምምነት የኤሌክትሪክ ሃይል ጣቢያዎች የማከፋፈልን አቅም በማሳደግ የሃይል መቆራረጥን ማስቀረት የሚያስችል ነው ሲሉ የኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሪት አዜብ አስናቀ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አስረድተዋል።
ለህንዱ ኩባንያ የሚከፋፈለው ገንዘብም 85 በመቶ ከፈረንሳይ የልማት ኤጀንሲ በብድር የሚሸፈን ሲሆን ቀሪው 15 በመቶ በመንግስት እንደሚሸፈንም ታውቋል።
በሃገሪቱ እየተባባሰ የመጣውን ይህንኑ የኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ተከትሎ በኢንዱስትሪው ዘርፍ ተሰማርተው የሚገኙ ኩባንያዎች በቅርቡ አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽ/ቤት በማቅረብ ውይይት ማካሄዳቸው የታወሳል።
መንግስት ባለፈው አመት ውሉን የጨረሰ የህንዱ ኩባንያ አጥጋቢ ውጤት ባለማሳየቱ ሳቢያ ስራው በኢትዮጵያውያን ይተካል ሲል ይፋ ማድረጉ የሚታወቅ ነው።