ወደታንዛኒያ የሚገቡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 21 ፥ 2008)

የታንዛኒያ መንግስት ከኢትዮጵያ በህገወጥ መንገድ ወደሃገሩ የሚገቡ ስደተኞች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ረቡዕ አስታወቀ።

ባለፉት ሶስት ወራት ብቻ ከ200 በላይ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ወደ ሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ መግባታቸውን ያስታወቀው የታንዛኒያ ፖሊስ በተያዘው ሳምንት ተጨማሪ ስድስት ኢትዮጵያውያን በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጿል።

ወደሃገሪቱ በህገወጥ መንገድ ገብተዋል የተባሉት ኢትዮጵያውያንም ከነገ በስቲያ አርብ ፍርድ ቤት ቀርበው ክስ እንደሚመሰረትባቸው ዘ-ጋርዲያን የተሰኘ የታንዛኒያ ጋዜጣ ዘግቧል።

ከቀናት በፊት በቁጥጥር ስር የዋሉት ስደተኛ ኢትዮጵያውያን እድሜያቸው በ18 እና 21 ክልል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን መዳረሻቸውም ደቡብ አፍሪካ እንደነበር ታውቋል።

ከታንዛኒያ በተጨማሪ የማላዊ እንዲሁም የዛምቢያ መንግስታት ወደሃገራቸው የሚገቡ ስደተኛ ኢትዮጵያውያን ቁጥር እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

የአለም አቀፉ ስደተኞች ድርጅት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን በየመን መውጫን አጥተው እንደሚገኙና ችግሩ እልባት ባላገኘበት ወቅት ወደ ሃገሪቱ የሚሰደዱ ኢትዮጵያውያንን ስጋት ፈጥሮ እንደሚገኝ ይፋ ማድረጉም ይታወሳል። በየዕለቱ በትንሹ 40 ስደተኛ ኢትዮጵያውያን የሚገቡባት ኬንያ በበኩላ በድንበር ዙሪያ የመቆጣጠሪያ ጣቢያዎቿን በማብዛት ከኢትዮጵያ የሚሰደዱ ሰዎችን ለመግታት ጥረት መጀመሯን ገልፃለች።

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ተከትሎ በርካታ ወጣቶች በመሰደድ ላይ መሆናቸውንም የተለያዩ አካላት አስታውቀዋል።