ኢሳት (መጋቢት 20 ፥ 2008)
አንድ የቻይና ኮንስትራክሽን ኩባንያ የመለስ ዜናዊ የአመራር አካዳሚን ዋና ጽ/ቤት ለመገንባት የ 1.3 ቢሊዮን ብራ ዋጋ ግምት አቀረበ።
የማዕከሉን ዋና ጽ/ቤት ለመገንባት ጨረታን ያወጣውና ማዕከሉን እያስተዳደረ ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የህንጻውን ሙሉ ወጪ እንደሚሸፍን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ከሶስት እስከ አራት ሄክታር በሚሆን መሬት ላይ ያርፋል የተባለው ይኸው የአካዳሚው ማዕከል በባለ ሰባትና 19 ፎቆች የሆኑ ዘጠኝ ህንጻዎች እንደሚኖሩትና ግንባታውም በቀጣዮቹ ሁለት አመታት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የህንጻውን ግንባታ ለማካሄድ በጨረታው የተሳተፉና በተለያዩ ምክንያቶች ውድቅ የተደረጉ የሃገር ውስጥ ኩባንያዎች በበኩላቸው የጨረታው ውጤትን በመቃወም ቅሬታን እንዳቀረቡም በሃገር ውስጥ ያሉ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ዮቴክ እና አፍሮ ጽዮን የተባሉ ሃገር በቀል የኮንስትራክሽን ተቋራጭ ድርጅቶች የጨረታውን ውጤት በመቃወም አቤቱታቸውን ለመንግስት አካል አቅርበው የሚገኙ ሲሆን ግዙፉን ህንጻ ለመገንባት ከ30 የሚበልጡ ኩባንያዎች ፍላጎት አሳይተው እንደነበር ታውቋል።
ይህንኑ አካዳሚ በሃላፊነት ሲመሩ የቆዩት የቀድሞ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ አዲሱ ለገሰ ከአራት ወር በፊት አቶ ቴዎድሮስ ሃጎስ በተባሉ የመንግስት ሃላፊ መሾማቸው የታወሳል።
የተለያዩ የመንግስት ሰራተኞችን በመንግስት ፖሊሲዎችና እቅዶች ዙሪያ ስልጠናን የሚሰጠው ማዕከሉ ባለፉት ሶስት አመታት ወደ 3ሺ የሚጠጉ ሲቢል ሰራተኞችን ማሰልጠኑንም ለመረዳት ተችሏል።
በአዲስ አበባ የሚቋቋሙ ሁለት ማዕከሎችን ጨምሮ ተመሳሳይ ማዕከሎችን በአማራ ኦሮሚያ፣ ትግራይና ደቡብ ክልሎች እንደሚቋቋሙም ተገልጿል።
አነስተኛ ዋጋ አቅርቧል የተባለው የቻይናው ኩባንያ ግንባታውን በቅርቡ ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን 1.5 እና 1.3 ቢሊዮን ብር ዋጋን አቅርበው ነበር የተባሉ የሃገር ውስጥ ኩባንያዎችም ጨረታው አጥጋቢ ባልሆነ መልኩ ውድቅ መደረጉን በመግለጽ ላይ ናቸው።