ኢሳት (መጋቢት 16 ፥ 2008)
የኢትዮጵያ መንግስት ትችት ሲቀርብበት በቆየው የመሬት ቅርምት ፕሮግራም ከሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት በላይ አንዱን ሄክታር በ20 ብር ሲሸጥ መቆየቱ ተገለጠ።
የስዊዘርላንድ ሃገርን ያክል የቆዳ ስፋት ያለው መሬትን ለሽያጭ አቅርቦ የነበረው መንግስት ባለፉት አምስት አመታት ብቻ ከ204 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለባለሃብቶች ማስረከቡን ሮይተርስ የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ አርብ ዘግቧል።
ለአለም አቀፍ ገበያ ቀርቦ ከነበረው 3.6 ሚሊዮን ሄክታር መሬት መካከልም ከ2.4 ሚሊዮን ሄክታር የሚበልጠው ለ5 ሺህ 7 መቶ ባለሃብቶች ተሸጦ የነበረ ሲሆን በዘርፉ የተገኘውም ውጤት የተጠበቀውን ያህል እንዳልሆነ ተነግሯል።
በርካታ አለም አቀፍ ተቋማት መንግስት ተግባራዊ ያደረገው ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎችን ለውጭ ባለሃብቶች የመስጠቱ ሂደት በአካባቢ እና በነዋሪዎች ዘንድ ተፅዕኖ ያመጣል ሲሉ ቅሬታ ማሰማታቸውንም ሮይተርስ በዘገባው አውስቷል።
ይሁንና፣ የመንግስት ባለስልጣናት እቅዱ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘትና የቴክኖሎጂ ሽግግርን እንዲሁም የግብርና ምርትን ለማሳደግ ታልሞ እንደነበር ይገልጻሉ።
ባለፈው አምስት አመታት ውስጥ ለባለሃብቶች ተሰጥተው ከነበሩት ከ2.4 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥም 30 በመቶ የሚሆነው ብቻ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣ የተቀረው የእርሻ መሬት ምንም አይነት ስራ ሳይከናወንበት መቅረቱም ታውቋል።
የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለተረከቡ ባለሃብቶች በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብን በብድር መልክ የሚያቀርብ ቢቆይም አብዛኛው ብድር የገባበት ሳይታወቅ መቅረቱንና መንግስት በዘርፉ ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰበት የባንኩ ባለስልጣናት ሰሞኑን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
የፌዴራል መንግስት ከወሰደው እርምጃ በተጨማሪም ክልሎች መሬት የመስጠት ፕሮግራሞቻቸውን በቅርቡ በተመሳሳይ ሁኔታ እንደሚያቆሙም የግብርና ልማት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ዳንዔል ዘነበ ለሮይተርስ ገልጸዋል።
በርካታ የሃገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች ከባንክ የወሰዱትን ብድር ሳይመልሱ ከሃገር የወጡ ሲሆን፣ የመንግስት ባለስልጣናት በዘርፉ የደረሰውን ጉዳይ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
ይሁንና በሃገር ደረጃ ደርሷል የተባለውን ችግር ለማጥናት በጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ ትዕዛዝ የተቋቋመ ቡድን በተለያዩ ክልሎች በመሰማራት ምርመራን እያካሄደ እንደሚገኝ ታውቋል።
መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገው የኦክላንድ ኢኒስቲቲዩትን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት የኢትዮጵያ መንግስት እያካሄደ ባለው የመሬት ቅርምት ፕሮግራም አርሶ አደሮችን ከቀያቸው ለማስለቀቅ በተካሄደው እንቅስቃሴ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል በሚል ቅሬታን ሲያቀርብ መቆየታቸው ይታወሳል።
ከጋምቤላ ክልል ወደ ጎረቤት ኬንያ የሸሹ አርሶ አደሮችም በመንግስት የሃይል እርምጃ እንደተወሰደባቸው ሲገልፁ መቆየታቸው መዘገቡ ይታወሳል።