አቶ ኤርሚያስ አመልጋ በዋስትና መፈታት ከፖሊስ በቀረበ ይግባኝ ታገደ

ኢሳት (መጋቢት 16 ፥ 2008)

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የአክሰስ ሪል ስቴት መስራችና ባለቤት በግማሽ ሚሊዮን ብር ዋስትና እንዲፈቱ የሰጠው ውሳኔ ከፖሊስ በቀረበ ይግባኝ ምክንያት ታገደ።

ፍርድ ቤቱ ፖሊስ ምርመራውን ለማጠናቀቅ የተሰጠው ጊዜ በቀና በህጉ መሰረት ነው በማለት የቀረበን ተቃውሞ ውድቅ በማድረግ አቶ ኤርሚያስ የዋስትና መብታቸው ተጠብቆ ከእስር እንዲለቀቁ መወሰኑ ይታወሳል።

ይሁንና፣ ፖሊስ የተሰጠውን ውሳኔ በመቃወም ይግባኝ ማቅረቡንና ተፈቅዶ የነበረውም ዋስትናም እንዲታገድ መደረጉን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።

ፍርድ ቤቱ ለአቶ ኤርሚያስ ዋስትናን ቢፈቅድም ከሃገር እንዳይወጡ ግን እገዳን ጥሎ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ፖሊስ አሁንም ድረስ ምርመራውን ለማካሄድ ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜን መጠየቁም ታውቋል።

የአክሰስ ሪል ስቴት መስራችና ባለቤት አቶ ኤርሚያስ፣ መንግስት ሰጥቷቸዋል የተባለን ያለመከሰስ መብት በመጠቀም ከሶስት ወር በፊት ከውጭ ሃገር ወደ ኢዲስ አበባ መመለሳቸው ይታወሳል።

ይሁንና፣ የኩባንያውን ጉዳይ የሚከታተሉ የመንግስት አካላት አቶ ኤርሚያስ በተሰጣቸው ጊዜ የገቡትን ቃል አልፈጸሙም በማለት ቅሬታን አቅርበው ፖሊስ ወንጀል ለመመስረት የሚያስችለውን ምርመራ እያካሄደ ይገኛል።

አቶ ኤርሚያስ አመልጋ ተሰማርተው በነበሩት የሪል ስቴት ስራ ጋር በተገናኘ የእምነት ማጉደልና የማታለል ወንጀልን ፈጽመዋል ተብለው በፖሊስ ምርመራ እየተካሄደባቸው መሆኑንም ይታወቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አቶ ኤርሚያስ በስድስት  ደረቅ ቼክ መፈረም በሚል የተመሰረተባቸው ክስ የፊታችን ሰኞ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሎም ይጠበቃል።

የአቶ ኤርሚያስ ጠበቆች በበኩላቸው መንግስት ለደንበኞቻቸው የሰጠውን ቃል በመጣስ ለእስር መዳረጉ ተገቢ አይደለም በማለት ቅሬታ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ይታወሳል።

ለእስር በመዳረጋቸው ከፍተኛ ኪሳራ እንደደረሰባቸው ለችሎት የገለጹት አቶ ኤርሚያስ በአሁን ሰዓት 20 ሺህ ብር ብቻ እንዳላቸውና በቤተሰብ ድጋፍ በመኖር መገደዳቸውን ባቀረቡት አቤቱታ አስታውቀዋል።