ወደ ደቡብ ምስራቃዊ ሱማሌ ግዛት ሲፈስ የነበረው የሸበሌ ወንዝ እንዲቆም ተደረገ

ኢሳት (መጋቢት 16 ፥ 2008)

በሶማሌ ክልል ያለው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ የክልሉ ባለስልጣናት ወደምስራቅ ደቡባዊ ሶማሊያ ግዛት የሚፈሰውን የሸበሌ ወንዝ ፍሰት እንዲቆም ማድረጋቸው ተገለጠ።

የወንዙ ፍሰት እንዲቆም መደረግን በወንዙ ላይ ህይወታቸው የተመሰረተ በርካታ ሶማሊያውያን ህይወት አደጋ ላይ እንደሚጥል የሶማሊያ መገናኛ ብዙሃን አርብ ዘግበዋል።

የሶማሌ ክልል አስተዳደር ሃላፊ የሆኑት አቶ አብዲ ሞሃመድ ኦመር የወንዙ ፍሰት እንዲቀር የተደረገው የመስኖና የግድብ ስራን ለማከናወን እንደሆነ መግለጻቸውን የሶማሊያ መገኛኛ ብዙሃን አስነብበዋል።

ይሁንና የወንዙ ፍሰት እንዲቆመ መደረግ 80 በመቶ የሚሆነው ህይወታቸው በወንዙ ላይ በተመሰረተው የሶማሊያ ደቡብ ምስራቃዊ ነዋሪዎች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ሸበሌ ሚዲያ ኔትዎርክ የተሰኘ የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

በክልሉ የሚገኙ በርካታ ዞኖች ወደረሃብ ለመሸጋገር አንድ ደረጃን ብቻ እንደቀራቸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በቅርቡ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በአካባቢው ያለን የድርቅ መባባስ ተከትሎም የክልሉ ባለስልጣናት የተረጂዎችን ህይወት ለመታደግ ርብርብን በማድረግ ላይ ሲሆን፣ የሸበሌ ወንዝ ፍሰት ለማስቀረትና ለመስኖ ጥቅም ማዋሉም በዚሁ እቅድ ውስጥ መካተቱ ታውቋል።

ይሁንና፣ የወንዙ ፍሰት እንዲቋረጥ መደረግ በታችኛው ተፋሰስ አካባቢ በሚኖሩ ነዋሪዎች ዘንድ የጥቅም ግጭትን ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩም ታዉቋል።

ለሃገሪቱ የሚቀርበው የእርዳታ እህል መዘግየትን ተከትሎ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ በቅርቡ ክፉኛ ጉዳትን ሊያደርስ እንደሚችል የተለያዩ አካላት ሲያሳስቡ መቆየታቸውም ይታወሳል።

በጅቡቲ ወደብ የእርዳታ እህልን የጫኑ እስር መርከቦች ጭነታቸውን ማውረድ ሳይችሉ በወደቡ ቀናቶችን እያስቆጠሩ እንደሚገኝ ብሉምበርግ የዜና አውታር ሃሙስ መዘገቡ ይታወቃል።

እነዚሁ መርከቦች የያዙትን የእርዳታ እህል ለማውረድ እስከ 40 ቀናቶች ሊወስድባቸው እንደሚችልም ባለስልጣናት ገልጸዋል።

የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው እርዳታው በአስቸኳይ ለተረጂዎች መቅረብ ካልቻለ ድርቁ የከፋ ጉዳትን ሊያደርስ ይችላል ሲሉ አሳስበዋል።