የእርዳታ እህል ጭነው ጅቡቲ የደረሱ 10 መርከቦች እህሉን ለማራገፍ 40 ቀን ሊጠብቁ እንደሚችሉ ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2015)

በኢትዮጵያ በድርቅ ለተጎዱ ተረጂዎች የሚደርስ የእርዳታ እህልን የያዙ አስር መርከቦች በጅቡቲ ወደብ የያዙትን የእርዳታ እህል ለማውረድ ተቸግረው እንደሚገኙ ተገለጠ።

እነዚሁ 45ሺ ቶን ያክል ስንዴን ይዘው ጎረቤት ጅቡቲ ወደብ የደረሱት መርከቦች የእርዳታ እህሉን ለማውረድ በትንሹ 40 ቀናቶች እንደሚፈጅባቸውም የወደቡ ባለስልጣናት ዋቢ በማድረግ ብሉም በርግ ዘግቧል።

አለም አቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች በበኩላቸው በሃገር ውስጥ ያለው የእርዳታ እህል ክምችት በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ውስጥ ሊያልቅ የሚችል በመሆኑ ጉዳዩ ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል።

ይሁንና በወደቡ ላይ ያለ የእቃ መጨናነቅ የእርዳታ እህሉን ለተረጂዎች በወቅቱ እንዳይደርስ አድርጎ የሚገኝ ሲሆን አስር የሚሆኑ መረከቦችም ከነእርዳታ እህላቸው ወረፋ እየተጠባበቁ እንደሆነ ታውቋል።

በአሁኑ ወቅት በጅቡቲ ወደብ የደረሰ የእርዳታ እህል በጥቅምት ወር ግዢ የተገዛ ሲሆን፣ በወደብ ያለው መጨናነቅ ለተረጂዎች ችግር መፍጠሩን የመንግስት ባለስልጣናት ገልጸዋል።

የእርዳታ እህሉን በወቅቱ አለመድረሱ የድርቁን አደጋ ሊያባብሰ እንደሚችል በኢትዮጵያ የብሪታኒያ የህጻናት አድን ድርጅት ተወካይ የሆኑት ጆን ግራም ለብሉምበርግ የዜና አውታር አስረድተዋል።

የአደጋ መከላከል ኤጀንሲ ሃላፊ የሆኑት አቶ ምትኩ ካሳ በበኩላቸው በወደብ የተፈጠረውን መጨናነቅ ለመቅረፍ ለእርዳታ እህልና ለማዳበሪያ ቅድሚያ እንዲሰጥ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ኣነዚሁ በወደብ ላይ ወረፋን እየተጠባበቁ የሚገኙት መርከቦች በቀን 3ሺ ቶን ስንዴ የማውረድ አቅም ቢኖራቸውም በተሽከርካሪ እጥረት የተነሳ በቂ ጭነት እየተነሳ አለመሆኑም ታውቋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች የእርዳታ ተቋማት በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ከቀጣዩ ወር ጀምሮ መልኩን እየቀየረ ሊሄድ ይችላል ሲሉ ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቅት ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ተጋልጠው የሚገኙ ሲሆን ከ15 ቀን በኋላ ለተረጂዎች የሚቀርብ የእህል እርዳታም ሊያልቅ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል።

በጅቡቲ ወደብ ወረፋን ኣየጠበቀ የሚገኘው የእርዳታ እህልም ወደ ሃገሪቱ በአስቸኳይ ካልገባ ተረጂዎቹ የከፋ ጉዳት ሊደርስባቸው ይችላል ተብሎ መሰጋቱን የእርዳታ ተቋማት በመግለጽ ላይ ናቸው።