ኢሳት (መጋቢት 15 ፥ 2015)
ኢትዮጵያን ጨምሮ 20 የአለማችን ሃገራት በከፋ የሳንባ ነቀርሳ (ቲቢ) በሽታ መፈረጃቸውን የአለም ጤና ድርጅት ሃሙስ አስታወቀ።
በየአመቱ መጋቢት 15 የሚከበረውን የቲቢ (TB) ቀን አስመልክቶ ሪፖርትን ያወጣው የጤና ድርጅቱ እነዚሁ 20 አገራት በበሽታው መዛመት የተነሳ የጤና መሰረተ ልማታቸው ፈተና አጋጥሞት እንደሚገኝ ገልጿል።
ባለፉት አስር አመታት በሃገሪቱ የበሽታውን መስፋፋት ለመቆጣጠር የተለያዩ ጥረቶች ቢያደርጉም አጥጋቢ ውጤት ሊገኝ አለመቻሉን የአለም ጤና ድርጅት በሪፖርቱ አስፍሯል።
በየዕለቱ የአራት ሺ ሰዎች ህይወትን እየቀጠፈ የሚገኘውን የቲቢ በሽታ በቀጣዮቹ 14 አመት ውስጥ ከአለም ለማጥፋት አለም አቀፍ ዘመቻ መክፈቱን ድርጅቱ አክሎ አመልክቷል።
ይሁንና ኢትዮጵያን ጨምሮ በ20 ሃገራት ውስጥ ያለው የበሽታው ሁኔታ ልዩ ትኩረትን የሚሻ እንደሆነ ያስታወቀው የጤና ድርጅቱ ባንግላዴሽ፣ ብራዚል፣ ቻይና፣ ህንድና፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ በሽታው ክፉኛ ጉዳትን እያደረሰባቸው ካሉ ሃገራት መካከል መሆናቸውንም አስታውቋል።
ፊሊፒንስ፣ ታንዛኒያ፣ ቤይትናም፣ ናይጀሪያ፣ እና ፓኪስታንም ከ20ዎቹ ሃገራት መካከል መፈረጃቸውን ለመረዳት ተችሏል።
አነስተኛ የጤና ሽፋን የቲቢ በሽታ መድሃኒት እየተላመደ መምጣትና የፖለቲካ ቁርጠኝነት በሽታውን ለመቆጣጠር በተደረገው ሄደት የራሳቸው አስተዋጽዖ አድርገው እንደሚገኙም ተገልጿል።
በየሃገሪቱ ያለው የኤችአቪ ኤይድስ ስርጭትም በሽታውን ለመግታት በተደረገው ጥረት እንቅፋት ሆነው መቀጠላቸውን የአለም ጤና ድርጅት በአመታዊ ሪፖርቱ አስፍሯል።