የመንግስት ወታደሮች ዳጋ እስጢፋኖስን ለመዝረፍ ያደረጉት ሙከራ ከሸፈ

መጋቢት ፲፭ (አሥራ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በጣና ሃይቅ መሃል በሚገኘው ታዋቂው የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም አርብ መጋቢት 9/2008 ዓም 5 ጀልባዎች ወደ ገዳሙ ክልል በመጠጋት አሳ ለማስገር እንደመጡ በመናገር ዘረፋ ለመፈጸም ሞክረው ነበር። የገዳሙ የጥበቃ ሰራተኞች በአካባቢው አሳ እንደማይጠመድ ሲነግሯቸው ከጥበቃ ሰራተኞቹ ጋር አላስፈላጊ እሰጣገባ ውስጥ ገብተው ከአካባቢው ሂደዋል፡፡
ግለሰቦቹ በድጋሜ መጋቢት 12/ 2008 8 ጀልባዎችን ይዘው ወደ ገዳሙ የተመለሱ ሲሆን፣ ከገዳሙ አስተዳዳሪዎች ጋር ውዝግብ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ የገዳሙ ዋና አስተዳዳሪ ለአካባቢው ህዝብ ጥሪ ማድረጋቸውንና ሶወቹም አሳ ለማስገር ነው የመጣነው በማለት አካባቢውን ወዲያውኑ ለቀው ሄደዋል።
ይሁን እንጅ የኢሳት የክልሉ ወኪላችን ታማኝ ምንጮችን ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው በተከሰተው የዘረፋ ሙከራ እጃቸው አሉበት የሚባሉት በቅርቡ ከስልጠና የወጡ ወታደሮች ሲሆኑ ፣ በዘረፋ ሙከራ የቤተ ክርስቲያኒቱ ዘበኛ በተደረገው የተኩስ ልውውጥ ተመቶ ህይወቱ አልፏል፡፡የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም አስተዳዳሪ አባ ብርሃኑ ትንሳኤ አርብ መጋቢት 12/2008 ዓ.ም በስምንት ጀልባዎች የተሳፈሩ ዘራፊዎች ወደ አካባቢው በመምጣት ድጋሚ የዘረፋ ሙከራ ሲያደርጉ ወደ ባህርዳር ከተማ የጀልባ ማህበራት በመደወል ችግር ላይ መሆናቸውን ተናግረው እርዳታ እንዲያደርጉላቸው መማጠናቸውን የገለጸው ዘጋቢያችን፣ የጀልባ ማህበሩ ሃላፊዎችም ለሚመለከታቸው የጸጥታ አካላት በመናገር እርዳታ እንዲደረግላቸው ቢያስታውቁም ፈጣን እርምጃ ባለመወሰዱ የአንድ ዘበኛ ህይወት ሊያልፍ ችሏል፡፡ የገዳሙ አስተዳዳሪ ስለዘራፊዎች ማንነት ምንም ዓይነት መግለጫ እንዳይሰጡ በመንግስት አካላት በመታገዳቸው ምንም ምላሽ ለመስጠት ፍላጎት የሌላቸው መሆኑም ታውቋል፡ ፡
የባህር ዳር ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሃይሌ አበበ ወደ ገዳሙ የተጓዙት በማህበር የተደራጁ አሳ አስጋሪዎች ናቸው ብለዋል።