መጋቢት ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የወልቃይት የአማራ ማንነት ጥያቄ አቅራቢዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ሊላይ ሲሳይ፣ ከጎንደር ከተማ ተንስተው ወደ ዳንሻ ሲያመሩ መንገድ ላይ በጥቁር ላንድ ክሩዘር መኪና ይጓዙ የነበሩ ሰዎች፣ ከሾፌሮች ጋር በመነጋገር አፍነው ከወሰዱዋቸው በሁዋላ የአካባቢው ህዝብ ባስነሳው ተቃውሞ፣ መንገዶች ላለፉር አራት ቀናት ተዘግተዋል። በዳንሻና በሶረቃ ትምህርት ቤቶች የተዘጉ ሲሆን፣ መረጃው ወደ ተለያዩ የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች እየተዛመተ፣ ህዝቡ ለተቃውሞ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ሁኔታው ያሳሰበው መንግስት የመከላከያ ሰራዊት አባላቱን ወደ አካባቢው በመላክ ህዝቡን ለማስፈራራት ሙከራ ቢያደርግም ፣ ህዝቡ ግን ” የታሰሩት ሳይፈቱ” ተቃውሞአችንን አናቆምም በማለቱ፣ መከላከያ ሰራዊቱ እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥቦ፣ የአገር ሽማግሌዎች ጣልቃ እንዲገቡ ተደርጓል።
የሰሜን ጎንደር ሃገረ ስብከት ሊቀጳጳስ አቡነ ኤልሳ ወደ ስፍራው ሄደው የተዘጉ መንገዶች እንዲከፈቱ ሲማጸኑ ውለዋል። በመጨረሻም ህዝቡ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ፣ መንገዶችን ዛሬ እንደከፈቱ በማድረጉ፣ በመንገድ መዘጋት ምክንያት ቆመው የነበሩ መኪኖች ለመንቀሳቀስ ችለዋል። ነዋሪዎች ለአቡኑ ያቀረቡት ቅድመ ሁኔታ ፣ አቶ ሊላይና ሌሎች የታሰሩ ሰዎች በሙሉ ተፈትተው፣ ወደ አካባቢያችን መጥተው ካላየናቸው፣ መንገዶችን መልሰን ዘግተን ተቃውሞአችንን እንቀጥላለን የሚል ሲሆን፣ አቡኑም ” ሰዎቹ ይፈታኑ፣ ካልተፈቱ መንገዶችን መልሳችሁ ትዘጋላችሁ፣ ይህንን አረጋግጥላችሁዋለሁ” ብለው ትናንት ምሽት ቃል መግባታቸውን ተከትሎ መንገዶች ተከፍተዋል። ይሁን እንጅ ይህን ዜና እሳከጠናከርንበት ሰአት ድረስ የታሰሩት ሰዎች ስለመለቀቃቸው የታወቀ ነገር የለም።
ዛሬ እኩለቀን ላይ በርካታ የመንግስት ባለስልጣናትን የያዙ መኪኖች አስመራ መንገድ በሚባለው አዲስ በተሰራው ጎዳና ወደ ኣዘዞ ከተማ ሲሄዱ መታየታቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል። መኪኖቹ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትን የያዙ ሲሆን፣ ከፍተኛ ወታደራዊ አጅብም ተደርጎላቸዋል። ወደ ዳንሻ ሲሄዱ ያልታዩት ባለስልጣናት፣ ሲመለሱ መታየታቸው የመንገዱን መከፈት ለማብሰር ሊሆን ይችላል ሲሉ ነዋሪዎች ግምታቸውን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል የአካባቢውን ህዝብ ትጥቅ ለማስፈታት የተጀመረው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞታል። መንግስት በአካባቢው በማንኛውም ጊዜ ግጭት ሊነሳ ይችላል የሚል ድምዳሜ ላይ የደረሰ ሲሆን፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች ትጥቅ የማስፈታቱን ስራ በጉልበት እንደሚገፋት በመናገር ላይ መሆኑን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
“የወልቃይት ጠገዴ ህዝብ ያለፍላጎቱ ወደ ትግራይ ክልል እንዲካለል ተደርጓል፣ የወልቃይት የአማራ ማንነቱ ይከበርለት በማለት የተጀመረው ተቃውሞ፣ በህወሃት ቁጥጥር ስር ለሚገኘው ኢህአዴግ ከፍተኛ ራስ ምታት ሆኖበታል። የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር ችግሩ በሶስት ወር ውስጥ ይፈታል የሚል መግለጫ የሰጠ ቢሆንም፣ እነዚህ አካባቢዎች ወደ አማራ ክልል ካልተካተቱ በስተቀር ችግሩ የሚቆም አይሆንም በማለት ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ወገኖች ተናግረዋል። ጥያቄውን የሚያቀርቡት የኮሚቴ አባላቱ በአሁኑ ሰአት ወደ ሶረቃና አጎራባች ከተሞች መንቀሳቀሳቸው ተውቋል።