በአርሲ አዳባ የመንግስት ካድሬዎች የሃይማኖት ግጭት ለማስነሳት ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር ተገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 13 ፥ 2008)

ከኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ጋር ተያይዞ በተነሳው ግጭት በአርሲ አዳባ ከተማ የመንግስት ካድሬዎች በሙስሊሞችና ክርስቲያኖች መካከል ግጭት ለማስነሳት ከፍተኛ ቅስቀሳ ሲያደርጉ እንደነበር በአካባቢ የሚኖሩ ኢሳት ያነጋገራቸው ሰዎች ገለጹ።

የመንግስት ካድሬዎች በመስጊድ ውስጥ ከአንድ ወር በፊት ለፈነዳው ቦምብ  ተጠያቂዎቹ “የአማራ ብሄር ተወላጆች” እንደሆኑ መስጊድ ውስጥ በመገኘት ሲቀሰቅሱ እንደነበር እማኞች ለኢሳት ገልጸዋል።

እነዚህ የመንግስት ካድሬዎች በኦሮሚያ በተቀሰቀሰው ግጭት  በመንግስት ሃይሎች የተገደሉትን ሶስት ሰዎችንም የገደሉት የአማራ ብሄር አባላት እንደሆኑ በመግለፅ የአዳባ ህዝብ በአዳባ ከተማ በሚኖር አማራ ላይ መነሳት እንዳለበት ሲቀሰቅሱ እንደነበር ለማወቅ ተችሏል።

ግርማ እና መኮንን የተባሉ የመንግስት ካድሬዎች “በአማራ ላይ እርምጃ መውሰድ አለባችሁ፣ አማሮች መስጊድ ላይ ቦምብ ስለወረወሩ በአጻፋው ሙስሊሙ ቤተክርስቲያናትን ማቃጠል አለበት” በማለት ህዝበ-ሙስሊሙን በአደባባይ ለመቀስቀስ ቢሞክሩም፣  የአካባቢው ህዝብ ግን በአዳባ ከተማ ለተፈጸመው የሶስት ሰዎች ግድያ የመንግስት ሃይሎች ተጠያቂ እንደሆኑና፣ የካድሬዎች ቅስቀሳ ተቀባይነት የሌለው ነው በማለቱ ግፍ እየደረሰበት እንደሚገኝ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለኢሳት በስልክ  ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ ከአራት ወር በፊት በኦሮሚያ በተቀሰቀሰው ግጭት ከ350 በላይ ሰዎች በመንግስት ሃይሎች እንደተገደሉና ከ5ሺ በላይ እንደታሰሩ የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ።