ኢሳት (መጋቢት 13 ፥ 2008)
በሳምንቱ መገባደጃ እሁድ በአማራ ክልል በዳንሻ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ማክሰኞ ለሶስተኛ ቀን መቀጠሉንና በአጎራባች ያሉ ነዋሪዎች ከወልቃይት ተወላጆች ጎን በመሰልፍ ላይ መሆናቸው እማኞች ለኢሳት ገለጡ። በሶሮቃ የሚገኙ የሃይማኖት አባቶችና ነዋሪዎች “ጥያቄው የእኛም ነው” በማለት ከወልቃይት ተወላጆች ጎን በመቆም ተቃውሞን እንደተቀላቀሉት ማክሰኞ ከስፍራው የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
በዳንሻና በሶሮቃ መንገዶች ተዘግተው መዋላቸውን የተናገሩት እማኞች በፀጥታ ሃይሎችና በወልቃይት ተወላጆች መካከል የተፈጠረው ውጥረት ተባብሶ መቀጠሉን ገልጸዋል።
ሰኞ በትግራይ ልዩ የጸጥታ ሃይሎችና በታጠቁ የወልቃይት ተወላጆች መካከል ሲካሄድ የነበረው የተኩስ እርምጃም እልባትን ያላገኘ ሲሆን፣ ተጨማሪ የፌዴራልና የክልል የጸጥታ ሃይሎችም በስፍራው በመሰማራት ላይ መሆናቸው ታውቋል።
ቁጥሩ ከፍተኛ የሆነ የፌዴራል ልዩ ሃይል ወደ ወልቃይት ጠገዴ በመሰማራት ላይ መሆኑም ለነዋሪዎች ስጋት ፈጥሮ እንደሚገኝ የአካባቢው እማኞች አስረድተዋል።
ሰኞ ሁለት የዳንሻ የወልቃይት ጠገዴ ኮሚቴ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ቁጥራቸው በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ነዋሪዎችም ለሶስተኛ ቀን ማክሰኞ መታሰራቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
የማንነት ጥያቄ በማቅረባችን ብቻ ኢሰብዓዊ ድርጊት እየተፈጸመብን ነው የሚሉት የአካባቢው ተወላጆች ጉዳይ የሚመለከተው የመንግስት አካል መፍትሄ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።
በቅርቡ በጉዳዩ ዙሪያ መገለጫን የሰጡ የመንግስት ባለስልጣናት የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ ህገ-መንግስታዊ ምላሽን አግኝቷል ሲል ለፓርላማ ሪፖርት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ይሁንና፣ የወልቃይት ጠገዴ ተወላጆች ከ20 አመት በፊት የተነሳው ህጋዊ ጥያቄን እልባትን ሳያገኝ ተጨማሪ ውጥረትን ፈጥሮ እንደሚገኝ ይገልጻሉ።
በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ ክልል አስተዳደራዊ ጥያቄን ያቀረቡ የኮንሶና አካባቢዋ ተወላጆች ከመንግስት ጋር አለመግባባት ውስጥ መሆናቸው ይታወቃል።