ኢሳት (መጋቢት 13 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ መንግስት 499ሺ ቶን ስንዴን ለመግዛት አለም አቀፍ ጨረታ ማወጣቱን ሮይተርስ የአውሮፓ የንግድ ተቋማት ዋቢ በማድረግ ማክሰኞ ዘገበ።
የእርዳታ ድርጅቶት በበኩላቸው ከሁለት ሳምንት በኋላ ለተረጂዎች የሚቀርብ እርዳታ ሊያልቅ የሚችል በመሆኑ ድርቁ የከፋ ጉዳት ማድረስ ይጀምራል ሲሉ በድጋሚ አሳስበዋል።
ከአለም አቅፍ ገበያ ተገዝቶ ወደሃሪቱ የሚገባው የስንዴ አቅርቦት በትንሹ 120 ቀናትን የሚፈጅ በመሆኑም ከ10 ሚሊዮን የሚበልጡ ተረጂዎች ለችግር ይጋለጣሉ ተብሎ ተሰግቷል።
ባለፈው ሳምንት አለም-አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በርካታ በድርቅ የተጎድ ዞኖች ለረሃብ አንድ ደረጃ በቀረው ሁኔታ ውስጥ መመዝገባቸውን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በተያዘው ሳምንት በመንግስት ለግዢ የቀረበው የስንዴ ጨረታም ከግንቦት ወር ጀምሮ እስከ ሃምሌ ወር ድረስ ወደ ሃገሪቱ ሊደርስ እንደሚችል የአውሮፓ የንግድ ኩባንያዎች ከሮይተርስ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት የመንግስት ባለስልጣናት የአለም-አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ የድርቅ አደጋን ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ሲሆነ፣ በእስካሁኑ ሂደትም ከሚፈለገው 1.4 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ ከግማሽ በታች የሚሆነው ብቻ መገኘቱ ታውቋል።