ኢሳት (መጋቢት 13 ፥ 2008)
በድርቅ በተጎዱ ክልሎች ከሚገኙ ትምህርት ቤቶች መካከል 75 በመቶ የሚሆኑት የውሃ አቅርቦት የሌላቸው መሆኑን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ማክሰኞ አስታውቋል።
አስር በመቶ ጭማሪን ያሳየው ይኸው የውሃ እጥረት ተማሪዎች በአግባቡ ትምህርታቸውን እንዳይከታተሉ አድርጎ እንደሚገኝም ድርጅቱ በድርቁ ዙሪያ በየሳምንቱ በሚያወጣው ሪፖርት ገልጿል።
በስድስት ክልሎች ውስጥ የሚገኙ ወደ አንድ ሚሊዮን አካባቢ ሰዎችም ካለባቸው የውሃ እጥረት የተነሳ ውሃን በተሽከርካሪ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ሲሆን 350ሺ የሚሆኑት ብቻ በትራንስፖርት መድረስ መቻሉን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አመልክቷል።
ለዚሁ ተግባር ከሚያስፈልጉ 432 የውሃ መያዣ ተሽከርካሪዎች መካከል 210 የሚሆኑት ብቻ በስራ ላይ ተሰማርተው እንደሚገኝም ድርጅቱ በሪፖርቱ አስፍሯል።
በድርቁ ምክንያት የዘር እህላቸውን ለተጠቀሙ አርሶ አደሮች የዘር እህል የማቅረቡ ስራም ከእርዳታው ጎን ለጎን አሳሳቢ ሆኖ መገኘቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
ለእነዚሁ አርሶ አደሮች የዘር እህልን ገዝቶ ለማከፋፈልም ከ60 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ድጋፍ ካልተገኘ በበልግ ወቅት አርሶ አደሮች የሚዘሩት እህል እንደማይኖር ድርጅቱ አሳስቧል።