መጋቢት ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በአሁኑ ወቅት ፌዴራል ፖሊስ ተጠሪነቱ ለፌዴራልና አርብቶአደር ልማት ሚ/ር ሲሆን አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ፖሊስን ለአንድ አስፈጻሚ መ/ቤት ብቻ ተጠሪ አድርጎ መቀጠል የአሰራር ክፍተት ይፈጥራል ተብሎ በመታሰቡ ወደፊት በጥናት ላይ ተመስርቶ እስኪወሰን የፌዴራል ፖሊስ ተጠሪነት ለጠ/ሚኒስትሩ እንዲሆን በረቂቅ አዋጁ ተደንግጎአል፡፡
በመሆኑም አሁን በስራ ላይ ያለው የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/2004 ተጠሪነት የሚመለከተው ድንጋጌ ለጠ/ሚኒስትሩ በሚል እንዲሻሻል ቀርቦአል፡፡
የብአዴኑ ነባር ታጋይ አቶ ካሳ ተክለብርሃን የፌደራልና አርብቶ አደር ልማት ሚኒስትር ሆነው በተሾሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ የፌደራል ፖሊስ ተጠሪነት እንዲለወጥ መደረጉ፣ የህወሃት እጅ አለበት የሚሉና በህወሃትና ብአዴን መካከል ያለው ልዩነት እየሰፋ መምጣቱን አመላካች ነው በማለት አስተያየቶች እየቀረቡ ነው።በኦሮሚያና በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እየተነሱ ያሉትን ሕዝባዊ ተቃውሞዎች ለመቆጣጠር አመቺ ሁኔታን ከመፍጠር ጋር የተያያዘ የፖለቲካ ውሳኔ ሊሆን ይችላል የሚሉ አስተያየቶች መሰንዘራቸውን ዘጋቢያችን ገልጿል። የፌደራል ፖሊስ መስሪያ ቤት በአብዛኛው በህወሃት ታጋዮች የተሞላ ነው።
በሌላ በኩል በፌዴራል የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮምሽን ፣በገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ፣በሸማቶችና በፍትሕ
ሚ/ር ስር ተበታትኖ ስራውን ያከናውን የነበረውን የአቃቤ ህግ መ/ቤት በአንድ ሚኒስቴር መ/ቤት በማደራጀት ሁሉንም ወጥነት ባለው መልኩ ለማገልገል ያሰችላል የተባለ ረቂቅ አዋጅ ለፓርላማው ቀርቦአል፡፡ አዲሱ ሚኒስቴር መ/ቤት የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ በመባል የሚታወቅ ሲሆን የቀረበው የማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በጸረ ሙስና ኮምሽን፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በሸማቶችና በፍትህ ሚኒስቴር ይቀርቡ የነበሩ ክስችን እንዲሁም በፍትሀብሔር ጉዳይ
መንግስት በመወከል በሀገር ውስጥ በዓለም አቀፍ የፍትህ መድረኮች ለመንቀሳቀስ ያሰችለዋል ተብሎአል፡፡የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ተጠሪነቱ ለጠ/ሚኒስትሩ እና ለሚኒስትሮች ም/ቤት በጣምራ መሆኑንም ረቂቅ አዋጁ
ያሳያል፡፡ የፌዴራል ማረሚያ ቤትም ከፌዴራልና አርብቶአደር ልማት ጉዳዮች ሚ/ር ስር ወጥቶ በፌዴራል ጠ/አቃቤ ህግ ስር እንዲሆንም በዚህ ረቂቅ አዋጅ ተደንግጎአል፡፡ ይህንንም ተከትሎ የአስፈጻሚ አካላትን ለመደንገግ የወጣው አዋጅ ማሻሻያ ቀርቦበታል፡፡
አዋጆቹ ለዝርዝር እይታ ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮምቴዎች ተመርተዋል፡፡