ኢሳት (መጋቢት 12 ፥ 2008)
ለአዲስ አበባ ከተማ የመጠጥ ውሃን ለሚያቀርበው ለገዳዲ የውሃ ግድብ ተጨማሪ ውሃን በማቅረብ ሲያገልግል የነበረው የድሬ ግድብ በቀጣዩ ወር ሙሉ ለሙሉ አገልግሎትን እንደሚያቋርት የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አስታወቀ።
የግድቡ አገልግሎት ማቋረጥም በከተማ ነዋሪዎች ዘንድ የከፋ የውሃ እጥረት እንዲከሰት እንደሚያደርግ ባለስልጣኑ አሳስቧል።
ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ከተማ የ24 ሰዓት የውሃ አገልግሎት የሚያገኙ ዋና ዋና አካባቢዎች ከተያዘው ሳምንት ጀምሮ ውሃን በፈረቃ እንደሚያገኙ ተገልጿል።
የለገዳዲ ግድብ የውሃ መጠን በመቀነስ ላይ መሆኑና ተጨማሪ ውሃን ለግድቡ የሚያቀርበው የድሬ ግድብ በቀጣዩ ወር ስራውን የሚያቆም በመሆኑ ውሃ እንዳያጡ ተደርገው የቆዩ አካባቢዎች ሁሉ በፈረቃው መካተታቸውን ባለስልጣኑ አስታውቋል።
እነዚሁ አካባቢዎች በሳምንት አራት ቀን ብቻ ውሃን የሚያገኙ ሲሆን የተቀሩ የከተማዋ ስፍራዎችም የውሃ እጥረት ችግራቸው የከፋ ሊሆን እንደሚችል ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
አለም አቀፍ ሆቴሎች፣ ተቋማትና በመኖሪያ አካባቢዎች ከተለመደው በተለየ መልኩ የውሃ እጥረቱ ተጽዕኖ እንደሚያሳድርባቸውም ይጠበቃል።
ከ19 አመት በፊት ለገዳዲ ግድብ ውሃን እንዲያቀርብ ታስቦ የተገነባው የድሬ ግድብ ሙሉ ለሙሉ ውሃን ማቅረብ ባለመቻሉ ምክንያት የክረምቱ ወቅት እስከሚገባ ድረስ በከተማዋ የውሃ እጥረቱ እንደማይፈታ የአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አክሎ ገልጿል።
የከተማዋ አብዛኛው ክፍል ካለፉት አራትና አምስት ወራቶች ወዲህ በከፍተኛ የውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት እጥረት ውስጥ መሆኑ ይታወቃል።
ከአራት አመት በፊት የአለም ባንክ የከተማዋን የውሃ አቅርቦት ለማሻሻል የ150 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍን ሰጥቶ የነበረ ሲሆን በዚሁ ፕሮግራም በአቃቂ-ቃሊቲ አካባቢ የከርሰ-ምድር ውሃ ፕሮጄክት ቢጀመርም፣ ፕሮጄክቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ አለመደረጉ ይነገራል።
ባንኩ በሰጠው ድጋፍም ሃዋሳ፣ ድሬዳዋን፣ ጎንደር፣ ጅማ ከተማና መቀሌ ታቅፈው እንደነበር ከባንኩ ከተገኘ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።