ዜጎች በርሃብ ምክንያት መሰደዳቸውን ቀጥለዋል

መጋቢት ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በኢትዮጵያ የሚታየውን ረሃብ መንግስት ለገጽታ ግንባታ በሚል ለመደበቅ ጥረት በማድረግ ላይ ቢሆንም፣ ዜጎች ግን የመንግስትን ከፍተኛ የጸጥታ ቁጥጥር እያለፉ ወደ ተለያዩ ከተሞች በመሰደድ ላይ ናቸው። ከዚህ ቀደም በታሪካቸው ድርቅ ጎብኝቷቸው የማያውቁት ቦታዎች ሳይቀሩ ረሃቡን መቋቋም ተስኖአቸው እየተሰደዱ ነው።
የአዲስ አበባው ወኪላችን ያነጋገራቸው አርሶአደር የሁለት ልጆች አባት ሲሆኑ ከሁለት ሳምንት በፊት እርሳቸውና ሌሎች 15 የሚሆኑ ሰዎች ከአዴት አካባቢ ተሰደው አዲስ አበባ ገብተዋል። አዴት ከተማ በምእራብ ጎጃም ዞን ውስጥ የምትገኘዋ ይልማና ዴንሳ ወረዳ ዋና ከተማ ስትሆን፣ ወረዳው በእህል ምርታቸው ከሚታወቁት የአማራ ክልል አካባቢዎች አንዱ ነው። ዛሬ ግን አርሶአደሩ ምርቱ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀነሱ፣ እንደ እርሳቸው ያለው ደሃ ስደትን አማራጭ አድርጎ እየወሰደ ነው። መንግስት እንዳይረዳን ከአቅሙ በላይ ሆኖበታል፤ እርዳታውም እዚህ ግባ የሚባል አይደለም የሚሉት አርሶ አደሩ፣ እንደዚህ የከፋ ዘመን እንዳላጋጠማቸው ይገልጻሉ።
ከሰሜን ወሎ መርሳ አካባቢ የመጡ ሶስት ሴቶች ደግሞ ፣ ረሃቡ ጠንቶባቸው ወደ አዲስ አበባ መሰደዳቸውን ይናገራሉ።
በአካባቢው ስላለው ድርቅ የአነጋጋርናቸው አንድ ታዋቂ ሰው በሰሜን ወሎና ደቡብ ወሎ በድርቅ የተጎዱ ቦታዎችን ሄደው በመጎብኘትና በችግር የተጠቁ ሰዎችን በማነጋገር እንደተናገሩት፣ በረሃቡ ሰዎች መሰደድ ብቻ ሳይሆን እየሞቱ ነው ። ረሃቡ፣ ሰቆጣ፣ ዳና ወረዳ፣ አላማጣ፣ ቆቦ፣ አጃ ፣ ምሆኒ ፣ ኮረም፣ ማይጨው፣ ከሃርቡ ወረዳም እንዲሁ ተሰደው ወደ ወልድያና ሌሎችም የአገሪቱ አካባቢዎች የሄዱ አሉ። በአላማጣ፣ የትግራይ ክልል የሚሰጠው እርዳታ ዘረኝነት የታከለበት ነው የሚሉትን ግለሰቡ፣ አማርኛ ለሚናገሩት እርዳታ ያልቀረበላቸው በመሆኑ ከብቶቻቸው እያለቁ ለመሆኑ ማስረጃ አለን ይላሉ። አንድ ለአምስት ለተደራጁት ብቻ እርዳታ እየተሰጠ መሆኑን፣ እንዲያውም የተበላሸ ቦሎቄ ተሰጥቷቸው ለሞት የተዳረጉ ሰዎች መሞታቸውን ገልጸዋል። ተሰደው ከሄዱት መካከል አንድ ሰው መንገድ ላይ ሞታ ማግኘታቸውንና መዘጋጃው እንደቀረበው ገልጸዋል። የውሃ ችግሩ በሁሉም የዞኑ ከተሞች የከፋ መሆኑንም አክለዋል ።
ደጋው የደቡብ ወሎ ክፍል ማለትም ደሴ ዙሪያ፣ ወይናምባ፣ ለጋንቦ እና ሌሎችም ተራራማ አካባቢዎች ለከፍተኛ ችግር ተዳርገው እየተሰደዱ ነው ።
መንግስት ተከታታይ የኢኮኖሚ እድገት ማግኘቱንና አገሪቱም በምግብ ራሱዋን ችላለች በማለት መግለጫ ሲሰጥ ቆይቷል። ረሃቡን በቁጥጥር ስር ማዋሉን በመግልጽ የውጭ አገር ድርጅቶች፣ ለራሳቸው ሲሉ ቁጥሩን እያጋነኑት ነው የሚል ወቀሳም ማቅረቡ በተደጋጋሚ ተዘግቧል። ይሁን እንጅ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ፣ የአለማቀፉ ማህበረሰብ ኢትዮጵያን ረስቷታል በማለት ወቀሳ አቅርበዋል። “እርዳታ ሊሰጠን ይገባል፣ ልንረሳ አይገባም፣ በአገራችን 750 ሺ የደቡብ ሱዳን ስደተኞችን ማስጠለላችን መዘንጋት የለበትም” ያሉት አቶ ሃይለማርያም፣ እርዳታ ሳይቀርብ ቀርቶ ለሚፈጠረው ማንኛውም ነገር የአለማቀፉ ማህበረሰብ በጊዜው ባለመድረሱ የተነሳ መሆኑን ማወቅ ይገባል” ሲሉ፣ ተጠያቂነቱን ወደ ውጭ አገር ለጋሽ አገራት አዙረውታል።
የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ የአለማቀፉ ማህበረሰብ የተረጅውን ቁጥር እያጋነኑ ማቅረባቸውን በመጥቀስ ወቀሳ ከማቅረባቸው በተጨማሪ፣ ረሃቡን በራሳቸው ጥረት በቁጥጥር ስር ማዋለቸውን በተነጋሩ በጥቂት ወራት ውስጥ፣ አቶ ሃይለማርያም እንደገና “አትርሱን” በማለት የተማጽኖ እና የማስጠንቀቂያ ደወል ማሰማታቸው ፣ በመንግስት ባለስልጣናት መካከል ያለው አለመናበብ እየሰፋ መምጣቱን ያሳያል ሲል ዘጋቢያችን አስተያየቱን አስፍሯል።