በደቡብ ኦሞ ዞን መሬትና የባንክ ብድር ከወሰዱት ባለሃብቶች መካከል ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑት የህወሃት አባላት ናቸው ተባለ

በደቡብ ኦሞ ዞን መሬትና የባንክ ብድር ከወሰዱት ባለሃብቶች መካከል ከ98 በመቶ በላይ የሚሆኑት የህወሃት አባላት ናቸው ተባለ
መጋቢት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የአካባቢው ተወላጅ ባለሙያዎች ከዞኑ ግብርና፣ የህብረት ስራና የኢንቨስትመንት ቢሮ ባለሙያዎች ያገኙትን መረጃ አጠናክረው ለኢሳት በላኩት ዝርዝር ሪፖርት እንዳመለከቱት ከ2006 ዓም ጀምሮ በደቡብ ክልል፣ በደቡብ ኦሞ ዞን 20 ኢንቨስተሮች ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህ መካከል 16 ቱ ወይም 80 በመቶው የህወሃት አባላት ወይም ደጋፊ የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ፣ 4ቱ ወይም 20 በመቶው ብቻ የአካባቢው ተወላጆች ናቸው። በክልሉ ለልማት በሚል ከተከፋፈለው 106 ሺ 997.7 ሄክታር መሬት ውስጥ 105 ሺ 914.6 ወይም 98.9 በመቶውን የህወሃት አባላትና ደጋፊ የጥቅም ተጋሪዎች የተቀራመቱት ሲሆን፣ የአካባቢው ተወላጅ ባለሀብቶች 1083 ሄክታር ወይም 1 በመቶ ብቻ የሚሆነውን መሬት ወስደዋል።
የህወሃት አባላት መሬቱን በማስያስ ለመሬት ዝግጅት በሚል ብቻ እስከ 635 ሚሊዮን 487 ሺ 600 ብር ብድር ሊቀበሉ እንደሚችሉና ይህንንም ገንዘብ በሌላ የሥራ መስክ በማዋል ሌላውን በትክክለኛ መንገድ የሚሰራ ዜጋ ከፉክክር እንሚያስወጡት ባለሙያዎች ተናግረዋል ፡፡በዞኑ ‹በስራ ላይ ዋለ ከተባለ› የወጣው ገንዘብ ከ5 ሚሊዮን 84 ሺህ ብር በታች እንደሆነና ቀሪው ከ630 ሚሊዮን ብር በላይ ወደ ዞኑ እንዳልመጣ፣ ይህም ከቀረጥ ነጻ ከሚገቡና በብድር ከሚወሰዱ የእርሻ መሳሪያዎች፣ተሽከሪካርዎችና ኬሚካሎች እንደማያካትት ተገልጿል።
የህወሃት ባለሀብቶች ከወሰዱት መሬት ወስጥ 95 ሺ 487 ሄክታር ወይም 89.2 በመቶ በስኳር ፕሮጀክት ቦታ አካባቢ መሆኑ ፣ እስካሁን አለሙ የተባለው ደግሞ ከ800 ሄክታር በታች መሆኑ፣ የአካባቢውን ህዝብ እያነጋገረ ነው።
ዞኑ ያለውን እምቅ ሃብት ተረድተው ወደ አካባቢው የመጡት ባለሃብቶች የአንድ አካባቢ ሰዎች ብቻ መሆናቸውና የሌሎች ብሄሮች አባላት የሌሉባቸው መሆኑ፣ ባለሀብት የተባሉት ግለሰቦች በህወሃት ደጋፍ እንደመጡ የሚያሳይ መሆኑን በጥናቱ ተጠቁሟል።
እነዚህ መሬት በብዛት የወሰዱ የህወሃት ባለሃብቶች ” የአገርና ህዝብ ሃብት በማስያዝ በዝቅተኛ ግምት ለመሬት ዝግጅት ብቻ ከ635 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መውሰዳቸው፣ የዞኑ ልማት፣የምግብ ምርትና የአካባቢው ነዋሪ ህይወት እንዲበደል፣ የአካባቢው ባለሃብቶች ወደ ምርት ኢንቬስትመንት የመግባት ተነሳሽነት ስሜት እንዲወድቅ፣ ሌሎች አልሚዎች ወደ ዞኑ ለመግባት የሚችሉበት ዕድል እንዲዘጋ አድርገዋል”የሚለው ጥናቱ፣ እነዚህን በአካባቢው የማይታወቁና ቋሚ አድራሻቸውን የማይገልጹ፣ እንዲሁም የድጋፍ ደብዳቤ ከሚፈልጉበት ጊዜ ውጪ በአካባቢው የማይታዩ የትግራይ ተወላጅ የህወሃት አባላት፣ የሃሰት ኢንቬስተሮች የተከለለላቸውን ቦታና የኢንቬስትመንት ፈቃድ በማሳየት ብድር እንዲሰጣቸው የትብብር ድጋፍ ደብዳቤ የተጻፈላቸው ፣ ጥቂት ቦታ ላይ ምንጣሮ ጀምረው አልምተናል በማለት የዞኑን ግብርናና ኢንቬስትመንት ቢሮ በሙስናና በማስፈራራት፣በማስመስከር ተጨማሪ ብድር እንዲሰጣቸው የሚያደርጉት አካሄድ፣ ችግሮችን አዝሎ የሚመጣ ነው ሲል ያስጠነቅቃል።
በዞኑ በሚገኙ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ ከፍተኛ መሬት የወሰዱት የህወሃት ድርጅቶችና የህወሃት ሸሪኮች ፣ በናጸማይ ወረዳ ኦሞ ሸለቆ አግሮ እንዱስትሪ፣ በኛንጋቶም ወረዳ፣ ሲሳይ ተስፋዬ አግሮ እንዱስትሪ እና ናሩስ ባዮ ቴክኖሎጂ፣ በዳሰነች ወረዳ ሉሲ እርሻ ልማት፣ በሳላመነ ወረዳ ኤኤቲ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና ጂ ዋይ ቢ ኤስ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ በናማጸይ ወረዳ ሳግላ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ በማሌ ወረዳ ኤን ቲ ኤስ ኢንተርናሽናል ፣ በዳሰነች ወረዳ ዳንኤል ፋሲል፣ በደቡብ አሪ ወረዳ አቶ አማኑኤል ገብረመድህን፣ በሃመር ወረዳ አቶ ረታ ሃይለምርያም፣ በዳሰነች ወረዳ መላ እርሻ ልማት፣ በኛንጋቶም ወረዳ ዶ/ር ጣችመ ሃጎስ፣ በኛንጋቶም ወረዳ አዳማ ዴቨሎፕመንት፣ በሳላማበ ወረዳ ሳትኮን ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል እርሻ ናቸው።
በአካባቢው ተወላጆች የተያዙት የእርሻ ድርጅቶች ጂንካ ደንና ቅመማ ቅመም፣ ገበየሁ ምናሉ፣ ተፈሪና ልጆቹ እርሻ ልማት እና ሱዳሜል እርሻ ብቻ ናቸው።
መረጃውን በተመለከተ የዞኑ አስተዳደር አስተያየቱን እንዲያካፍለን በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ሊሳካልን አልቻለም።
በዚህ ዞን ውስጥ በሚኖሩ በሱርማ ማህበረሰብ አባላት ላይ የክልሉ ልዩ ሃይል የወሰደው እርምጃ ኢትዮጵያውያንን ማስደንገጡ ይታወቃል።