አቶ ካሳ ተክለብርሃን “መንግስት ችግር አለብኝ፣አርሙኝ ማለቱ ውድቀቱን አያሳይም” አሉ

መጋቢት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የፌደራል ጉዳዮችና አርብቶአደሮች አካባቢ ልማት ሚኒስትር አቶ ካሳ ተክለብርሃን መንግስት ችግር አለብኝ፣አርሙኝ ማለቱ እንደውድቀት እንደማይታይ ተናግረዋል።
ሚኒስትሩ ከመንግስታዊው አዲስዘመን ጋዜጣ የመጋቢት 8/2008 ዓም እትም ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ መንግስት ይሄ ችግር አለብኝ ብሎ አርሙኝ፣ አስተካክሉኝ፣ማለቱ ታላቅነት ነው፣ውድቀት አይደለም ብለዋል።
አንዳንዶች መንግስት ጉድለት አለብኝ ስላለ መምራት አይችልም፣ወድቆአል በማለት የህብረተሰቡን ስሜቶች ወደሌላ ለመውሰድ የሚፈልጉ ሀይሎች አሉ፣ይህን በጥንቃቄ ማየት አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
እርስበርሳችን በፍቅር መዋደድ፣ መከባበር ይገባናል ያሉት አቶ ካሳ፣ ትምክህትና ጠባብ አመለካከት ካለ ማስወገድ ይገባናል ብለዋል።
በሌላ በኩል በኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄ መልስ አግኝቶአል፣ የሚቀርቡ ጥያቄዎች ከማንነት ጋር አይያያዙም የሚሉት ሚኒስትሩ ፣ በዚሁ ቃለመጠይቅ ላይ እስከዛሬ ለፌዴሬሽን ም/ቤት ከቀረቡት የማንነት ጥያቄዎች በደቡብ ክልል የስልጤ፣በአማራ የቅማንት ትክክለኛ በመሆኑ ምላሽ አግኝቶአል በማለት እርስበርሱ የሚጋጭ መግለጫ ሰጥተዋል።
አቶ ሐይለማርያም ደሳለኝም ሰሞኑን ለፓርላማ አባላት በኢትዮጵያ የማንነት ጥያቄ ምላሽ አግኝቷል በማለት እርስ በርስ የሚጋጭ መግለጫ ሰጥተዋል።