መጋቢት ፰ (ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ዲላ በውሃ ችግር ከተመታች ወራት ቢቆጠሩም፣ ችግሩ ግን እስካሁን አልተቀረፈም። በአካባቢው ጋሪ ያላቸው ሰዎች ውሃ ከወንዝ በመቅዳት ለከተማው ህዝብ እየሸጡ፣ የውሃ ችግሩን ለመቅረፍ ጥረት ቢያደርጉም፣ የከተማው መስተዳደር ግን፣ የውሃ ችግሩን ሳይቀርፍ፣ ውሃ ሻጮች ውሃ ከወንዝ አትቀዱም በማለት ክልከላ አስቀምጧል። በዚህ የተበሳጩት ከ70 በላይ የሚሆኑ ውሃ ነጋዴዎች፣ ጋሪዎቻቸውን አሰልፈው ሰላማዊ ሰልፍ አድርገዋል። ውሃ ቀጅዎቹ ወደ መስተዳድሩ በመሄድ ጥያቄ ቢያቀርቡም የሚሰማቸው አላገኙም። በከተማው የሚታየው ከፍተኛ የውሃ እጥረት የአካባቢውን ነዋሪዎች ለውሃ ወለድ በሽታ ዳርጓቸዋል። በዲላ ተሰልፈው የሚታዩት የውሃ ጀሪካኖች ከተማዋን እንደ ሰቆጣ ሁሉ ቢጫዋ ከተማ የሚል ስያሜ አሰጥቷታል።