ኢሳት (መጋቢት 7 ፥ 2008)
የአለም አቀፍ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ መንግስት ለሰብዓዊ መብት መከበር በሚታገሉ ተቋማትና ግለሰቦች ላይ የሚወስደውን የእስራትና የአፈና ድርጊት እንዲያቆም ግፊትን እንዲያደርጉ መቀመጫውን በዚህ በአሜሪካ ያደረገው የኦክላንድ ኢንስቲቲዩት ጥሪን አቀረበ።
ከአንድ አመት በፊት ለእስር የተዳረጉ ሶስት የመሬትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦችም ለቀረበባቸው የሽብርተኛ ወንጀል ክስ ምንም አይነት ማስረጃ ሳይቅረብላቸው እየተንገላቱ መሆኑን ተቋሙ አውስቷል።
ኦሞት ኦግዋ፣ አሽኒ ኦስቲን እና ጀማል ኦማር የተባሉ የጋምቤላ አካባቢ ተወላጆች በክልሉ ያለን የመሬት ቅርምትና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ትኩረት እንዲያገኝ በማድረጋቸው ምክንያት ለእስር መዳረጋቸው ይታወሳል።
የሶስቱ ግለሰቦችን የመብት ጥሰት ያወሳው ኦክላንድ ኢንስትዩት ሌሎች የፖለቲካ አመራሮችና አባላት እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን አባላት በተመሳሳይ የመብት ረገጣ ውስጥ እንደሚገኙ አመልክቷል።
የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ብሪታንያ፣ ጀርመን እንዲሁም የአውሮፓ ህብረትና የአለም ባንክ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ግፊትን በማድረግ እየወሰደ ያለውን የአፈናና የእስር ድርጊት እንዲያቆም ሚናቸውን መጫወት እንዳለባቸው ኦክላንድ ኢንስቲትዩት አሳስቧል።
በሃገሪቱ ያሉ የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ ጥሪውን ያቀረበው ይኸው አለም አቀፍ ተቋም ሰብዓዊ መብትና አካባቢን ለመከላከል አይደለም ሲል ባቀረበው ጥሪ አስተላልፏል።
የኢንስቲትዩቱ የበላይ ሃላፊ የሆኑት አኑራዳህ ሚታል የኢትዮጵያ መንግስት የጸረ-ሽብር አዋጁን በመሳሪያነት በመጠቀም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን እያፈነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዚሁ ዘመቻም ባለፉት ጥቂት አመታት በርካታ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት፣ ጋዜጠኞች እንዲሁም ተማሪዎችና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ግለሰቦች ለእስር መዳረጋቸውን የተቋሙ ሃላፊ አስታውቀዋል።
የኦክላንድ ኢንስቲትዩት በጋምቤላ ክልል ከመሬት ቅርምት ጋር የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አለም አቀፍ ትኩረትን እንዲያገኙ በማድረግ የአለም ባንክና የብሪታኒያ መንግስት እርምጃን እንዲወስዱ ማድረጉ ይታወሳል።
ይከው ተቋም ባካሄደው አለም አቀፍ ዘመቻም የአለም ባንክ በጉዳዩ ዙሪያ ማጣራት እንዲካሄድ አድርጎ በሚሰጠው ድጋፍ ላይ የማስተካከያ እርምጃን የወሰደ ሲሆን፣ የብሪታኒያ መንግስትም በባንኩ በኩል በየአመቱ የሚሰጠውን አንድ ቢሊዮን ዶላር አካባቢ ድጋፍ እንዲቋረጥ ማድረጉ ይታወቃል።
የኦክላንድ ኢንስቲትዩት በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በማስመልከት ለአምስት የኢትዮጵያ የልማት አጋር ሃገራትና የፋይናንስ ተቋማት ጥሪውን ማቅረቡንም ለመረዳት ተችሏል።