ኢሳት (መጋቢት 7 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ እየተባባሰ መምጣትን ተከትሎ መንግስትና ዓለም-አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ተጨማሪ የእርዳታ ጥሪ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ሮይተርስ ዘገበ።
የዘር እህል እርዳታን የሚፈልጉ አርሶ አደሮች ቁጥርም ከ2.2 ሚሊዮን ወደ 3.3. ሚሊዮን ማሻቀቡንና የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የዜና አውታሩ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
ከሁለት ወር በፊት በተደረገ የእርዳታ ጥሪ 1.4. ቢሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ተገልጾ የነበረ ሲሆን፣ የተረጂዎች ቁጥር መጨመረንና የእርዳታ አቅርቦት መጓተትን ተከትሎ አዲስና ተጨማሪ የእርዳታ ጥሪ ማቅረብ እንዳስፈለገ የተባበሩት መንግስታት የእርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ አስታውቀዋል።
ከተለያዩ አካላት የተውጣጡ ባለሙያዎችም ለሶስት ሳምንት የሚቆይ የዳሰሳ ጥናት እያካሄዱ እንደሚገኙ ታውቋል።
በሃገሪቱ ተከስቶ ያለውን የድርቅ መባባስ ተከትሎም ከዚህ ቀደም ለእርዳታ ያልተመዘገቡ ሰዎች ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ መጋለጣቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።
በተያዘው ወር መጨረሻ ላይ ይፋ ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቀው አዲስ የእርዳታ ጥሪም የተረጂዎችን ቁጥር ወደ 15 ሚሊዮን ሊደርስ ይችላል ተብሎ የተሰጋ ሲሆነ፣ ድርቁን ለመቋቋምም ከሁለት ቢሊዮን ዶላር በላይ እንደሚያስፈልግ ይጠበቃል።
በመጀመሪያ ዙር ለቀረበው የ1.4 ቢሊዮን ዶላር ጥሪ የተገኘው ምላሽ ከግማሽ በታች ሲሆን፣ የተረጅዎች ቁጥር ግን እያደገ መምጣቱን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል።
ሃገሪቱ ያቀረበችው የእርዳታ ጥሪም ከሶሪያና የመን ቀጥሎ በአለም ሶስተኛ ሆኖ መመዝገቡን ለመረዳት ተችሏል።
ይኸው የድርቅ አደጋም በኢትዮጵያ ታሪክ በ50 አመት ውስጥ የከፋ ሆኖ መገኘቱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ይገልጻል።