ዩኒሴፍ ዋና ዳይሬክተር የተከሰተው የድርቅ አደጋ ለመገምገም ኢትዮጵያን እየጎበኙ ነው

ኢሳት (መጋቢት 7 ፥ 2008)

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት (ዩኒሴፍ) ዋና ዳይሬክተር አንቶኒ ሌከን በኢትዮጵያ ያለውን የድርቅ አደጋ ለመታዘብ በሃገሪቱ ጉብኝትን እያደረጉ እንደሆነ ድርጅቱ ረቡዕ ገልጿል።

በድርቁ ክፉኛ ጉዳይ በደረሰባቸው ህጻናት ስጋቱን በተደጋጋሚ በመግለጽ ላይ ያለው የህጻናት መርጃ ድርጅቱ ክፉኛ የምግብ እጥረት ጉዳት የደረሰባቸውን ህጻናት ለመታደግ 100 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልገው ይፋ አድርጓል።

በድርቁ ምክንያት ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ ከተጋለጡት ከ10 ሚሊዮን በላይ ሰዎች መካከል አምስት ሚሊዮን የሚሆኑ ህጻናት ሲሆን፣ ግማሽ ሚሊዮን ያህሉ በምግብ እጥረት የተነሳ ክፉኛ የአካልና የጤና ጉዳት ድርሶባቸው እንደሚገኝ ታውቋል።

የአለም አቀፍ እርዳታ መዘግየትም በነዚሁ ህጻናት ላይ የሞት አደጋን ሊያስከትል ይችላል ተብሎ ስጋት መኖሩን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።

ከዚሁ ከድርቅ ዘገባ ጋር በተገናኘም የጠቅላይ-ሚንስትሩ አካማሪ የሆኑት አቶ አርከበ እቁባይ ሃገሪቱ በምግብ ምርት እራሷን የቻለች ሃገር ሆናለች ሲሉ ከብሉምበርግ የዜና አውታር ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ ገልጸዋል።

“ራሳችንን መመገብ ችለናል ሲሉ የተናገሩት አቶ አርከበ 95 ሚሊዮን አካባቢ የሚደረሰው የሃገሪቱ ዜጋ በምግብ ምርት ራሱን ችሎ እንደሚገኝ በድርቁ ዙሪያ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አስታውቀዋል።