መጋቢት ፯ (ሰባት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በክልሉ በመካሄድ ላይ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ በማስመልከት ኢሳት ያነጋገራቸው የቦረና ዞን የሰማያዊ ፓርቲ ተወካይ አቶ ጌታቸው በቀለ እንዲሁም በጉጂ ዞን እስካሁን የቀጠለውን ተቃውሞ ከሚያስተባብሩት መካከል አንድ ግለሰብ እንዳሉት በክልሉ የሚታየው ህዝባዊ እምቢተኝነት፣ መሰረታዊ የሆነው የፍትህና የነጻነት ጥያቄ እስከሚመለስ ይቀጥላል።
በሁለቱም ዞኖች እስከዛሬ ድረስ ውጥረትና ተቃውሞ እንዳለ ገልጸው፣ በአካባቢያቸው የሰፈረው የአጋዚ ጦር ውጥረቱን እያባባሰው ነው ይላሉ።
ህዝቡ 25 አመታት ሙሉ ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ ሲገልጽ መቆየቱን ያስታወሱት አቶ ጌታቸው፣ ህዝቡ ወደ ተቃውሞ የገባው እነዚህ ጥያቄዎች እንደመለሱ በመፈለግ ቢሆንም፣ ኢህአዴግ የህዝቡን ጥያቄ በአግባቡ መመለስ ሲገባው ወደ ሃይል እርምጃ ገብቷል ብለዋል::
አቶ ጌታቸው መንግስት በየጊዜው የተምታታ መልስ እየሰጠ መሆኑን ያስታወሱት ይህም አሳፋሪና የኢትዮጵያን ህዝብ ከመናቅ የሚመነጭ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ ንቃተ-ህሊና ከገዢው በላይ መሆኑን የገለጹት አቶ ጌታቸው፣ የህዝቡን የመብት ጥያቄ በእስራትና በግድያ መመለስ አይቻልም ብለዋል።
ጥፋት አጥፍተናል ካሉ፣ ካሳ መክፈል፣ የታሰሩትን መፍታት፣ እና ችግር የፈጠሩትን ለፍርድ ማቅረብ ነበረባቸው፣ ይህን ሳያደርጉ አጥፍተናል ማለት ህዝብን መናቅ ነው የሚሉት አቶ ጌታቸው፣ መንግስት ካለፉት 25 አመታት ልምድ ትምህርት ያገኘ አይመስለኝም፣ አሁንም ችግሩን በጉልበት ለመፍታት እየሞከረ በመሆኑ ውጥረቱን አባብሶታል ሲሉ አክለዋል ። በጉጂ ዞን የሚታየው ህዝባዊ እምቢተኝነት እንደቀጠለ መሆኑን የሚናገሩት የአካባቢው ተወካይ፣ ህዝቡ የተለያዩ እቅዶችን በመንደፍ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይላሉ። ህዝባዊ እምቢተኝነቱን ቤት በመዝጋት፣ ከስራ በመቅረት፣ ገበያ በመቅረት ህዝቡን ከስር በማደራጀት ተቃውሞው መቀጠሉን የገለጹት አስተባበሪው፣ ትግሉ ከላይ ወደታች የሚወርድ ሳይሆን፣ ከታች ወደ ላይ የሚሄድ ነው ብለዋል።
የሼክ አላሙዲን ንብረት የሆነው ሚዲሮክ ወርቅ ከአካባቢው እንዲለቅ ላቀረቡት ጥያቄ ፣ የክልሉ መንግስት ከአቅሜ በላይ ነው ያለ ሲሆን፣ ህዝቡ ኦኮቴ የሚባለውን ሁለተኛውን የወርቅ ማእድን ቦታ ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ መቆየቱንና አጋዚ ጦር መጥቶ ማስለቀቁን ተናግረዋል። ህዝቡ ትግሉን ቀጥሎአል የሚሉት አስተባበሪው፣ “ህዝቡ አንድነትና ነጻነት ይፈልጋል፤ ከሰሜን እስከደቡብ፣ ከምስራቅ እስከምእራብ ህዝቡ በዘር መከፋፈሉን ትታችሁ በአንድነት ታገሉ እያለ መሆኑን አክለው ተናግረዋል
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፈው እሁድ ማታ በቡሌ ሆራ ዞን በቅሊንሶ ራሳ ቀበሌ ውስጥ 10 ፖሊሶች በህዝቡ ላይ ድብደባ መፈጸማቸውን ተከትሎ ህዝቡ በወሰደው የአጸፋ እርምጃ፣ ፖሊሶች ሸሽተው ካመለጡ በሁዋላ፣ በማግስቱ ሃይላቸውን አጠናክረው ተመልሰው ድብደባ የፈጸሙ ሲሆን፣ 25 ሰዎችንም ይዘው አስረዋል። ከእነዚህ መካከል 13 ትናንት የተፈቱ ሲሆን፣ ቀሪዎቹ ለመጋቢት 8 ቀን 2008 ዓም ለፍርድ ተቀጥረዋል።