በአዲስ አበባ የ4 ልጆች አባት በፖሊሶች ተገደሉ

ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2008)

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ የሆኑ የ4 ልጆች አባት አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ በፖሊሶች ተገደሉ። ገዳዮቹ ፖሊሶች ጥቃቱን ያደረሱት በድብደባ መሆኑንም የአይን ምስክሮች ገልጸዋል።

አቶ ሽመልስ ፋሲል የተባሉ የአዲስ አበባ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ መሿለኪያ አካባቢ ነዋሪ የሆኑት ግለሰብ ዕሁድ ምሽት በሶስት የፖሊስ አባላት በደረሰባቸው ድብደባ ህይወታቸው አልፏል።

ድብደባውን ያደረሱት ፖሊሶች ድርጊቱን የፈጸሙት በሟች መኖሪያ ቤት ፊት ለፊት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ሟች ህይወታቸውን ያጡት በፖሊሶቹና በሌሎች ግለሰቦች መካከል የተፈጠረውን ግጭት በመገላገል ላይ ሳሉ እንደነበርም የአይን ምስክሮች ለኢሳት ገልጸዋል።

ፖሊሶቹ በአካባቢው በተደጋጋሚ ጥቃት ሲያደርሱ መቆየታቸውንና በዚህም ጥርሳቸው የተሰበረባቸው የአካባቢው ነዋሪዎችም መኖራቸው ተመልክቷል።

የ4 ልጆች አባትና የቡና እግር ኳስ ቡድን ደጋፊ በሆኑት በአቶ ሺመልስ ፋሲል ላይ ግድያውን የፈጸሙት ሶስቱ ፖሊሶች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለሟች ቤተሰብ የተነገረ ሲሆን፣ የት እንደታሰሩ ግን የታወቀ ነገር የለም። የአቶ ሽመልስ ፋሲል ህብረትን ተከትሎ ግድያው ከቡና እግር ኳስ ቡድን ደጋፊነታቸ ጋር ተያይዙ ቢነገርም፣ ኢሳት በደረሰው መረጃ ማጣራት ግድያው በፖሊሶች የዕብሪት እርምጃ መሆኑ ተመልክቷል።