የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎችን የማፈን እርምጃ አጠናክሮ እንደቀጠለ ሂውማን ራይትስ ዎች ገለጸ

ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2008)

የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን በነጻነት ለመግለጽ በሚፈልጉ የሃገሪቱ ዜጎች ላይ የሚወስደውን የአፈና እርምጃ አጠናክሮ መቀጠሉን ሂውማን ራይትስ ዎች ማክሰኞ ገለጠ።

የመንግስት የልማት ፖሊሲዎችና እቅዶች ዙሪያ እንኳን ትችትን የሚያቀርቡ ሰዎች መሳሪያ ያነገቡ ሃይሎችን ትደግፋላችሁ የሚል ክስ እየቀረበባቸው ለእስር በመዳረግ ላይ እንደሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ አስታውቋል።

ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ተቃውሞ ጋር በተገናኘ በኦሮሚያ ክልል የተቀሰቀሰውን ተቃውሞና መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ በዋቢነት በዝርዝር ያቀረበው ድርጅቱ ተግባራዊ ተደርጎ የሚገኘው የጸረ-ሽብር አዋጅ ህጉ ለዚህ አላማ ማስፈጸሚያ እየዋለ መሆኑንም ገልጿል።

በመንግስት ላይ ትችትን የሚያቅረቡ ከባድ ስቃይ እንደሚፈጸምባቸው ያወሳው ሂውማን ራይትስ ዎች ምንም አይነት ክስ ሳይመሰረትባቸው ለረጅም ጊዜ በእስር ቤት የሚሰቃዩ ሰዎች መኖራቸውንም ይፋ አድርጓል።

በሃገሪቱ ያሉ ፍርድ ቤቶችም ታሳሪዎች ላይ የሚፈጸሙ ስቃዮችን መርምረው እንደሚያውቁ የሚናገሩት የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ሃላፊዎች ታሳሪዎች ባልሰሩት ወንጀል በአቃቢ ህግ ክስ እየቅረበባቸው እንደሚንገላቱ አስታውቀዋል።

ሃገሪቱ ኢኮኖሚያዊና የልማት እድገትን አስመዝግባለች ቢባልም ዜጎች ሃሳባቸውን በነጻነት መግለፅ እስካልቻሉ ድረስ እድገቱ አጠያያቂ እንደሚሆን በሂውማን ራይትስ ዎች የሰብዓዊ መብት ተመራማሪ የሆኑት ፊሊክስ ሆርን ባቅረቡት ሪፖርት አስፍረዋል።

በሃገሪቱ ያሉ መገናኛ ብዙሃን በመንግስት አፈና ስር በመሆናቸው ምክንያትም የፀጥታ ሃይሎች በኦሮሚያ ክልል እንዲሁም በአጠቃላይ በሃገሪቱ እየወሰዱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በአግባቡ ማወቅ እንዳልተቻለም ሂውማን ራይትስ ዎች አክሎ አስረድቷል።

ሶስተኛ ወሩን ዘልቆ የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል ኣየተካሄደ ያለው ተቃውሞ ከ300 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች መሞት ምክንያት መሆኑም ሲገለጽ ቆይቷል።